“ከወጡት ስራዎቼ ይልቅ ገና የሚወጡት ናቸው ትልቅ ቦታ ያላቸው” አለማየሁ ገላጋይ

በዓስር ዓመታት ውስጥ 11 መፅሐፎችን የፃፈው ደራሲና ኃያሲ አለማየሁ ገላጋይ በጠንካራ ማሕበራዊ ሕይወቱ፣ በኃያሲነቱ እና አዳዲስ ነገሮችን ሞካሪ መሆኑን ብዙዎች ይመሰክራሉ።
"ከጎረቤቶቼ ከጓደኞቼ ጋር ካልሆንኩ፣ ካላሳለፍኩ፣ ዘግቼ የምቀመጥ ከሆነ እንዴት መፃፍ እችላለሁ?" ሲል የሚጠይቀው አለማየሁ "ብቸኝነት በራሱ የምታስባቸውን ነገሮች ይወስናል ፤ ለአንድ ደራሲ ዘጠና በመቶ መፃፍ ስራው ነው ብዬ አላስብም" ይላል።
አንድ ደራሲ ቲያትር መመልከት እንዲሁም ሲኒማ ማየት አለበት የሚለው አለማየሁ ሰውን ሳይለዩ ከማንኛውም ሰው ጋር ማሳለፍ በተለየ ለደራሲ አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራል።
በተለይ ልብወለድ የሚፅፍ ሰው እንደ ሳይንቲስት ወይም የሒሳብ ሊቅ በአንድ ነገር ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም የሚለው አለማየሁ ዙሪያ ገቡን የሚያውቅ የተሟላ አለም መፍጠር እንዲችል አለም የያዘቻቸውን በሙሉ ቀምሶ የሚያጣጥም መሆን ስላለበት ከሰዎች ጋር በማሳለፍ የሕይወት ልምዱን ማስፋት እንዳለበትም ይናገራል።
"እናም እኔ ከወዳጆቼ እና ጎረቤቶቼ ጋር ሳሳልፍ ለስራው እንደሚከፈል መስዋእትነት ነው" ሲል ያክላል።
አለማየሁ በቀን ውሎው ከወዳጆቹ ጋር አሳልፎ ለሊት ከ ዘጠኝ ሰአት በኋላ በመነሳት የማንበብ ፣ የመፃፍ አልያም ደግሞ በጥሞና የመመሰጥ ልምድ እንዳለው ይናገራል።
"ብዙ ጊዜ የምፅፈው ሁለት አመትም ሆነ አንድ አመት ያብሰለሰልኳቸውን ነው። እነዚህን በወረቀት ላይ ለማስፈር አንድ ወር፣ ሐያ ስምንት ቀን፣ ምናልባት 25 ቀን ቢፈጅብኝ ነው። ስለዚህ ቀሪውን ጊዜ ለወዳጅ ዘመድ አተርፋለሁ ስለዚህ አልቸገርም" ይላል።
የትኛውን ስራውን የበለጠ ይወዳል
አለማየሁ ከስራዎቹ ሁሉ ጥሩ የሚለው ቀጥሎ የሚፅፈውን ነው። "የፃፍኳቸውን ልብ ወለዶች መለስ ብዬ ማየት አልችልም ፤ እንዳውም አልወዳቸውም ማለት ይቻላል" ይላል።
ለውይይት እንኳ ሲቀርቡ በስራዎቹ ላይ አንተርሰው የሚነግሩኝ ነገር እንጂ ስለስራዎቹ የሚነግሩኝን አልወድም ይላል።
ፅፎ ከጨረሰም በኋላም የአርትኦት ስራ የሚሰሩለት ሌሎች መሆናቸውን የሚናገረው አለማየሁ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመታተሙ በፊት ሁለቴ ያነበበው 'በፍቅር ስም' የሚለውን መፅሐፉን ብቻ ነው።
"ያኔም ግፊት ስለነበር ነው፣ ከአሁን በኋላም ሁለቴ ከማንበብ ፈጣሪ ይጠብቀኝ" ሲል ያክላል።
የዛሬ ሁለት ወር የሚወጣ አዲስ መፅሐፍ ፅፎ መጨረሱን የሚናገረው አለማየሁ "ይህ መፅሐፍ አሁን ስለሚወጣ እወደዋለሁ ማለት አይደለም ከሱ የሚቀጥለውን ለመፃፍ እየተዘጋጀሁ ስለሆነ ይህንን የሚያነቡ ምን ይሉኛል ስል ነው የምጨነቀው"ሲል ያስረዳል።
"ወደ ኋላ የምንመለከት ከሆነ ወደፊት ለመጓዝ ያስቸግራል" የሚለው አለማየሁ ስራዎቹ የሌሎች ሰዎች ሆነው ምናለ ደጋግሜ ባነበብኳቸው የሚል ምኞት አለው።
አለማየሁ ሥነጽሑፍን ያስተማሩት ሰዎች አንድ ሰው መፃፍ ያለበት እድሜው አርባ አመት ሲሞላው በሕይወት ልምድ ሲካብት ነው እንዳሉት ያስታውሳል።
"በርግጥ እነርሱም ይህንን ከአርስቶትል ነው የወሰዱት። እኔም ጅል ስለሆንኩ የእነርሱን ምክር ተከትዬ የመጀመሪያ ስራዬ የሆነውን አጥቢያን ያሳተምኩት ልክ አርባ አመት ሲሞላኝ የዛሬ አስር አመት ነበር።" ሲል ያስታውሳል።
በዚህ 10 አመት ውስጥ 11 መፅሐፎችን የፃፈውም አባከንኳቸው የሚላቸውን ጊዜዎች ለማካካስ እንደሆነ ይናገራል።
"በዚህ ፌስ ቡኩ፣ በዚህ ኢንተርኔቱ ቀልብ ያሳጣል በዚህ ፈጣን ዘመን ቶሎ ቶሎ ካልፃፍኩ ምን ሊውጠኝ ነው።" ይላል
አንድ ደራሲ ለአንድ ሐገር ሲሰጥ በረከት ነው ብሎ እንደሚያምን የሚናገረው አለማየሁ "አለመፃፌ መክሊትን እንደመቅበር ነው። እንደመቅሰፍት አየዋለሁ" ይላል።
ለሚቀጥለው ትውልድ የነበረበትን ዘመን አንፀባርቆ ማለፍ አለብኝ ብሎ እንደሚያስብም ይናገራል።
የቋንቋው ከባድነት
በድርሰቶቹ ውስጥ የቋንቋው ውበት እና ምጥቀት በድርሰቱ ውስጥ የሚነሱ ሀሳቦቹን እንዳይረዱ እንቅፋት ነው የሚሉ አስተያየቶች ከአንባቢዎች የሚመጡ ሲሆን ይህንንም በተመለከተ
"ቋንቋዬ ይከብዳል አልልም። እንዳውም ወደ ፊት የሚመጣው ይከብዳል ነው የምለው" ይላል።
"መጉደል ይታየኛል ጊዜና ሁኔታዎች ቢገጣጠሙልኝ ጎንደር ጎጃም ወሎ እየሄድኩ የጎደለኝን ሞልቼ ብመለስ ስል አስባለሁ" ይላል።
የተወሰነ ጊዜ የተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች በመቀመጥ የሀገሩን ባህል እንዲሁም የቋንቋውን ውበት ቀስሞ በስራዎቹ ውስጥ ለመጠቀም ዘወትር እንደሚያስብ ይናገራል።
"አንድ ደራሲ ቋንቋውን ላክብድ ወይም ላቅልል ብሎ ማክበድም ማቅለል አይችልም" የሚለው አለማየሁ "ያ ከሆነ ተፈጥሮአዊ አይሆንም"ይላል።
ጎስቋላ ገፀባሕርያት
በስራዎቹ ውስጥ ጎስቋላ ገፀባህሪያት መኖራቸው የህይወቱ ነፀብራቅ እንደሆነ አለማየሁ ያስረዳል።
"የኖርኩት ቁርስ ተበልቶ ምሳ የማይበላበት ምሳ ከተበላ እራት የማይደገምበት አካባቢ ነው። በስራዎቼ ያንን ሕይወት ማሳየት ካልቻልኩ አስቸጋሪ ነው" ይላል።
የሐብትን ኑሮ አላውቀውም የሚለው አለማየሁ "የኖርኩበት እየመረጥኩም የምኖረው ሕይወት ይህንኑ ስለሆነ ፤ የማውቀውን ነው የምፅፈው" ሲል ይናገራል።
በመፅሐፎቹ ውስጥ በገፀባሕሪነት የተሳሉ አብዛኞቹም ከህይወቱ የተጨለፉ እንደሆነ የሚናገረው አለማየሁ
"አብሬ የኖርኳቸው የዘመን አሻራ የሆኑ እድሜዬን የተሳተፉ ናቸው።" አንዳንዴ በስራዎቹ ውስጥ በአንድ ገፀባሕሪ ውስጥ ተዳብለው የሚመጡ ሲሆን አንዳንዴ ደግሞ በእውኑ አለም ካለ ሰው ላይ ተጎርደው ይመጣሉ ሲል ያብራራል።
የኖረበትን አካባቢ ገፀባህሪያት በአንድ ላይ ፅፎ አስቀምጦ እሱ እንኳ ባይችል ሌሎች ቢፅፏቸው ደስ እንደሚለውም አለማየሁ ይናገራል።
"ነባር መንደሮች ሕይወታቸው ተመሳሳይ ስለሆነ ሌላ አካባቢ ያለው ኑሮ በድርሰቴ ውስጥ ከተሳለው ጋር ተመሳስሎባቸው ይሀኛው ገፀባህሪ እኛ ሰፈር ያለውን ሰው ይመስላል የሚሉ አንባቢያን እንደገጠሙት ይናገራል። እናቶቻችን ተመሳሳይ ናቸው፤ የአባቶቻችን ግድየለሽነት ተመሳሳይ ነው ስለዚህ አንባቢ ሲያነብ የኔን መንደር ብቻ ሳይሆን የእርሱን አካባቢ ሰው የሚመስሉ ቢያገኝ የፃፍኩት ዘመኑን ስለሆነ ነው" ይላል።
አንዳንዴ ልብወለዶች ወደታሪክነት ይቀየራሉ የሚለው አለማየሁ በፈጣን ለውጥ ውስጥ የሚፈርሱትን መንደሮች ሕይወት ተፅፎ ለታሪክነት መቅረት እንዳለበትም ያምናል።
"መንደሮች ሲፈርሱ እኮ የሰው ልጅ ነው አብሮ የሚፈርሰው። ሳይሞት ወደ መቃብር እንደወረደ ሰው እየው። ይህንን ነው ፅፎ ቢቻል ታሪክ አድርጎ ማስቀረት። ይህ የዘመን እዳ ነው፤ የኔ ዘመን እዳ፤ እንዴት ይህን እዳዬን ሳልከፍል ሳልፅፍ እቀራለሁ?" ሲል ይቆጫል።
ድርሰትና ሒስ
ከማህበረሰቡ ጋር ደራሲዎች ሲኖሩ የሚታዩትንና የሚሰሙትን ቅሬታዎች መግለፅ እንዳለበትም ያምናል።
"ይህ እዳ መክፈያም ጭምር ነው" ይላል። ራሱንም እንደ ህዝብ ወገንተኛ እንደሚያይም ይናገራል።
''የምኖርበትን አካባቢ ሳየው ከሚፈርስባቸው ወገን ስለሆንኩ ለብዙሃን ይጠቅማል የምለውን ሳልፈራ እሰነዝራለሁ፤ ፖለቲካ ባትሔድ ይመጣብሃል ሸሽተህ የትም አትደርስም" ይላል።
በደርግ ወቅት የሶሻሊዝም ርዕዮተ-ዓለምን የሚደግፉ እንደነ በአሉ ግርማ የመሳሰሉ ፀሀፊዎች ይፅፉ ነበር የሚለው አለማየሁ በዚህም ስርዓት ከሱ ተቃራኒ ስርዓቱን ደግፎ የሚፅፍ ሰው ቢያገኝ ሌላኛውን እይታ ማንፀባረቅ ይቻላልም ብሎ ያምናል።
ተስፋ መቁረጥ
አለማየሁ በደራሲነቱ ተስፋ የቆረጠበት ወቅቶች እንደነበሩ ይናገራል።
"የደራሲነት አንዱ ግዴታ እስኪመስል ድረስ መፅሐፍ ሻጮች ገንዘቤን እንዲሰጡኝ ለምኜ አውቃለሁ" ይላል።
የመፅሀፍ ሻጮች ማጉላላት እንደሚያሳምመው የሚናገረው አለማየሁ ለአሳታሚ እና ለአከፋፋይ ለመደወል ብዙ ጊዜ ይሳቀቅም ነበር።
ጭቅጭቁም አሰላችቶት አላሳትምም ብሎ ተስፋ የቆረጠበትም ጊዜ እንደነበር ይገልፃል።
ከበፍቅር ስም በኋላም ራሱ ማሳተም በመጀመሩ ብዙ ለውጥ እንዳየም ይናገራል።
የገቢውም ሁኔታ እንደተሻሻለ ይገልፃል።
በጎ ተፅዕኖ
በወዲያኛው ዘመን ከነበሩ ደራሲያን ያመለጠኝ በአሉ ግርማ ብቻ ነው የሚለው አለማየሁ ከበርካታ ትልልቅ የሀገሪቷ ደራሲያን ጋር አብሮ በማሳለፉ ከነሱም ብዙ እንደተማረም ይናገራል።
ከስብሐት ገብረእግዚአብሔር የመጨረሻ የሕይወት ዘመኖቹም አብሮ ከማሳለፉ በተጨማሪ እነ አበራ ለማ፣ አስፋው ዳምጤ፣ አብደላ እዝራ፣ የሺጥላ መኮንን፣ ደበበ ሰይፉ ስልጠና ስለሰጡት በሱ ህይወት ላይ ተፅእኖ መፍጠር ችለዋል።
"ከእነርሱ በተጨማሪ ስራዎቻቸውን ማንበቤ እና በደንብ መመርመሬ አብጠርጥሬ ለመተቸት መቻሌ እንዲሁም መፅሐፍ መፃፌ ረድቶኛል" ይላል።
"እኔ ሁሌም የምፎካከረው ከወደቀው ደራሲ ጋር አይደለም የሚለው አለማየሁ ፉክክሬ ከነሀዲስ አለማየሁ እና ከነበአሉ ግርማ ጋር ነው" ሲል ሃሳቡን ይቋጫል።