"ከሶማሌ ክልል ሸሽተን መጥተን አሁንም ሽሽት ላይ ነን"

በሀማሬሳ ላይ ተፈናቃዮች

በሐረር ከተማ አቅራቢያ በሐማሬሳ የመጠለያ ካምፕ ውስጥ የሚገኙት ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ኦሮሞዎች በመከላከያ ሰራዊት በተከፈተ ተኩስ የስድስት ሰዎች ሕይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ ብዙዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"በመጠለያ ውስጥ የሚበላ እና የሚጠጣ እየተጠባበቀ የሚገኘው ሕዝብ ላይ የተፈፀመው ግድያ ሐዘናችንን አባብሶታል።" ሲል መጠለያ ውስጥ ከሚኖሩት መካከል አንዱ የሆነው አሕመዲን ተማም ተናግረዋል።

"በተኩስ ወጥተን በተኩስ ተቀበሉን" የሚለት የመጠለያው ነዋሪ አህመዲን ከትናንት ጀምሮ ተኩሱን በመሸሽ ተደብቀው እንደሚገኙ ይናገራሉ።

የተፈናቃዮቹ ሰላም መደፍረስ ዋና ምክንያት የመከላከያዎቹ ድርጊት እንደሆነም ተናግረዋል።

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ጀማል አመዴ በበኩላቸው በተከሰተው ችግር አራት ሰዎች መሞታቸውንና አስራ አንድ ሰዎች ለጉዳት መዳረጋቸውን ተናግረዋል።

አቶ ጀማል ሆነ አቶ አህመዲን ይህ ሁኔታ በምን ምክንያት እንደተፈጠረ ሲያስረዱም "ከአዲስ አበባ ወደ ሶማሌ ክልል እየተጓዘ ያለ ተሳቢ መኪና እንዲፈተሽ በክልሉ ፖሊሶችና በወጣቶቹ ጥያቄ ሲቀርብ ወዲያውኑ ከየት እንደመጣ የማይታወቅ የመከላከያ ኃይል በህዝቡ ላይ የተኩስ እሩምታ ከፍተዋል" ሲሉም ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰአት በኦሮሚያ ፖሊሶች ሲጠበቅ የነበረው የስደተኞቹ መጠለያ በሀገር መከላከያ እየተጠበቀ መሆኑን የሚናገሩት አቶ አህመዲን አንዳንዶቹም ሸሽተው እየወጡም እንደሆነ ገልፀዋል።

"ከሶማሌ ክልል ሸሽተን ወጣን አሁንም በሽሽት ላይ ሽሽት ተጨምሮብናል። ከመንግስት አካልም የደረሰልን ማንም የለም" በማለት አቶ አህመዲን ብሶታቸውን ይገልጻሉ።

በተጨማሪም አቶ አህመዲን እንደሚገልፁት "መከላከያዎቹ እንደደረሱ ተጠላዮቹ ካምፑን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ ዛቻ ደርሶብናል።" የሚሉት አቶ አህመዲን የክልሉ መንግስት በአስቸኳይ እንዲደርስላቸው ጠይቀዋል።

ሌላኛው በካምፕ ውስጥ የሚገኝ ተፈናቃይ ሄይረዲን "የአሁነኛው በደል ያልተጠበቀ ነበር" በማለት ብሶቱን ለቢቢሲ ተናግሯል።

"የኮንትሮባንድ እቃ ጭኖ የነበረውን መኪና እንዲፈተሽ ሲጠይቁ በመኪና ውስጥ የነበሩት ሰዎች ለመከላከያ በመደወላቸው መከላከያዎቹ ደርሰው ይህንን በደል አድርሰዋል" ብሏል።

የመከላከያ ኃይሉም እንደደረሰ ጉዳዩን ከማረጋጋት ይልቅ ተኩስ እንደከፈተ የሚናገረው ሄይረዲን " የመጠለያ ቦታውን ጠብቁ የነበሩ የክልል ፖሊሶች የመከላከያ ሰራዊቱ ወደ ግቢ እንዳይገቡ ለመከላከል በጣሩበት ወቅት በተመሳሳይ በተከፈተባቸው ተኩስ የአንድ ፖሊስ ህይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ ሌላኛው ላይ ጉዳት ደርሷል" ብሏል ሄይረዲን።

ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በህይወት ፋናና በጀጎል ሆስፒታሎች እየታከሙ መሆናቸውም ተገልጿል።

በህይወት ፋና ሆስፒታል የጤና ባለሙያ የሆነው አለማየሁ ከፈኒ በበኩሉ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታሉ ለመጡት የመጀመሪየህክምና እርዳታ ቢደረግላቸውም እንኳ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው እንዲያገግሙ ተጨማሪ ህክምና እንደሚያስፈልጋቸው ይናገራል።

"እዚህ ለህክምና የመጡት በቀጥታ የተተኮሰባቸው ናቸው። አንዳንዶቹ ሆዳቸው ላይ እግራቸው፣ ጭንቅላታቸው፣ ወገባቸው ላይ በጥይት በመመታታቸው የተለያየ ህክምናዎችን እየሰጠን እንገኛለን" ይላል አቶ አለማየሁ።

በመሆኑም የመከላከያ ሰራዊቱ ግቢውን ለቆ በክልሉ ጥበቃ እንዲተካ እና የስደተኞቹም መጠለያ ሰላም ወደነበረበት እንዲመለስ አቶ አለማየሁ ጠይቋል።

"ተቸግረው በመጠለያ ውስጥ በሚገኙ ሰዎች ላይ ለሌላ ተጨማሪ ችግር መዳረግ ሌላ ብሶት ስለሆነ በጣም አዝነናል። በህዝብ ላይ የተፈፀመው ድርጊት በህግ ይታያል ከአሁን በኋላ በሰዎች መብት ላይ መጫወት ትክክል አይሆንም ጉዳት የደረሰባቸውም በሆስፒታል ህክምና እተደረገላቸው ነው "በማለት አቶ ጀማል የተሰማቸውን ኃዘን ገልፀዋል።

ተያያዥ ርዕሶች