የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በሙስና ሊከሰሱ ነው

Israeli Prime Minister Benjamin Netanyahu attends a cabinet meeting at the Prime Minister's office in Jerusalem on February 11, 2018.

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

የእስራኤል ፖሊስ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሙስና ሊከሰሱ ይገባል ብሏል።

ፖሊስ እንደገለፀው በጉቦ፣ በማጭበርበር እንዲሁም እምነትን በመጣስ ለመክሰስ በቂ መረጃ እንዳለው ነው።

በሀገሪቷ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው የተናገሩት ኔታንያሁ በበኩላቸው እነዚህ ውንጀላዎች መሰረት እንደሌላቸውና በጠቅላይ ሚኒስትርነታቸውም እንደሚቀጥሉበት ነው።

ውንጀላውም "ያለምንም መረጃ ይቆማል" ብለዋል።

ውንጀላዎቹ ምንድንናቸው?

አንደኛው የተነሳባቸው ጉዳይ አንድ የእስራኤል ጋዜጣ በአዎንታዊ መልክ ስለሳቸው እንዲዘግብ አድርገዋል ነው።

እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ የህትመቱ አዘጋጅም ክስ እንደሚጠብቃቸው ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል።

ሁለተኛው ውንጀላም ወደ 300 ሺ ዶላር የሚያወጣ ስጦታ ከታዋቂው ባለሀብትና በሆሊውድ ታዋቂ የፊልም ኩባንያ ባለቤትና አርኖን ሚልቻንና ከሌሎች ደጋፊዎቻቸው ተቀብለዋል የሚል ነው።

ጀሩሳሌም ፖስት እንደዘገበው እንደዘገበው ስጦታዎቹ ሻምፓኝ፣ ሲጋራና ሌሎች ሲሆኑ በምላሹም አርኖን የአሜሪካ ቪዛ እንዲያገኙ አመቻችተዋል የሚል ነው።

አርኖን የ'ፋይት ክለብ'፣ 'ጎን ገርል'ና 'ዘ ሬቨናንት' የሚባሉ ታዋቂ ፊልሞች ባለቤት ሲሆኑ ፖሊስም በጉቦ ሊከሰሱ ይገባል ብሏል።

ፖሊስ ጨምሮ እንደገለፀውም ኔታንያሁ ስጦታውን ከተቀበሉ በኋላ የአርኖን ሚልቻን ህግ እንዲፀድቅ ግፊት አድርገዋል ይላል።

ይህም ከአስራኤል ውጭ የሚኖሩ እስራኤላውያን ሀገራቸው በሚመለሱበት ጊዜ ለአስር ዓመታት ከግብር ነፃ እንዲሆኑ ነው። ይህ ረቂቅም በገንዘብ ሚኒስትሩ ውድቅ ተደርጓል።

ከዚህ በተጨማሪ ከአውስትራሊያዊው ቢሊየነር ጄምስ ፓከር ጋር በተያያዘ በማጭበርበር እንዲሁም እምነትን በመጣስ ተጠርጣሪ እንደሆኑ ፓሊስ ጨምሮ ገልጿል።

የእስራኤሉ ቻናል 10 የተባለው ሚዲያ እንደዘገበውም ቢሊየነሩ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለባለቤታቸው ስጦታ እንደሰጡ ለመርማሪዎች እንደተናገሩ ነው።

የእስራኤል ሚዲያዎች በተጨማሪ እንደዘገቡትም ኔታንያሁ በመርማሪዎች ቢያንስ ሰባት ጊዜ እንደተጠየቁ ነው።

ከዚህ በኋላ ምን ይፈጠራል?

ኔታንያሁ ይከሰሱ ወይስ አይከሰሱ በሚለው ሁኔታ የመጨረሻ ውሳኔን ለመስጠት ወደ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ይመራል።

የፍትህ ሚኒስትሩ አየለት ሻኬድ እንዳሉት ማንኛውም ጠቅላይ ሚኒስትር ስለተከሰሰ ብቻ ለመልቀቅ መገደድ የለበትም ብለዋል።

የኔታንያሁ ምላሽ

"በባለፉት ዓመታት ከ15 በላይ የሚሆኑ ምርመራዎችን አስተናግጃለሁ" በማለት በቴሌቪዥን ቀርበው ተናግረዋል።

" አንዳንዶቹም እንዳሁኑ በፖሊሶች መባረቅ ነው የተጠናቀቀው። እነዚህ ሙከራዎች ሁሉ ወደየትም አይሄዱም" ብለዋል።

የ68ዓመቱ ኔታንያሁ በሁለተኛ የጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው በማገልገል ላይ ሲሆኑ በዚህም ወቅት ብዙ ውንጀላዎችን አስተናግደዋል።