በዛሬው ዕለት እርስዎ የፍቅረኞችን ቀን ያከብራሉ? ለምን?

እምቡጥ ቀይ የጽጌሬዳ አበባዎች Image copyright Getty Images

ባለፉት የተወሰኑ ዓመታት በፍቅረኞች ቀን ወቅት በሱቅ መስኮቶች ላይ የሚለጠፉት የልብ ቅርጾች፣ ከተማዋን የሚያጥለቀልቋት የአበባ አይነቶችን መመልከት የተለየ ድባብ ይፈጥራል።

በሌላ በኩል ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶቸና ኬክ ቤቶችም ቢሆኑ ያሏቸውን ልዩ የሚሏቸውን አቅራቦቶች ለፍቅረኞችና ለፍቅረኛሞች በተመደበው ቀን ያዘጋጃሉ። የምሽት ቤቶችና 'ላውንጆች'ም እንዲሁ ታዋቂና ተወዳጅ አርቲስቶችን ከወይን ጠጅና ከልዩ ምግብ ጋር ይዘው ይቀርባሉ።

በዚህ ዓመት በ የካቲት7 ያረፈው 'ሴንት ቫለንታይንስ' በመባል የሚታወቀው ይህ የፍቅረኛሞች ቀን ቀይና ጥቁር ተለብሶ፣ ቀይ ጽጌሬዳና ቸኮሌት በመሰጣጣት በፍቅረኛሞች የሚከበር ነው። ይህ ባሕል ከምዕራባውያን የተወረሰ ቢሆንም ቢያንስ ባለፉት 6 ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያም ትኩረት እየተሰጠው መሆኑን ብዙ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

Image copyright Getty Images

የእናቶቻችንና ያባቶቻችን ዘመንስ?

የ62 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋና የድረሬዳዋ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ መሰሉ መዝለቂያ በጊዜያቸው የነበረውን ሁኔታ በማስታወስ ''ማክበሩ ቀርቶ ሴንት ቫለንታይንስ ምን እንደሆነም አላውቅም ነበር። በኛ ጊዜ እንኳን የፍቅረኛሞችን ቀን ልናከብር ስለፍቅር ብናስብ እንደ ወንጀል ነበር የሚቆጠርብን። ለነገሩ እኛ የኢህአፓ አባል ስለነበርን ቅድሚያ የሰጠነው ለትግሉ ነው። ከትግሉም ወደጋብቻ ገባን ብዙ ስለፍቅር የማሰቢያም ጊዜ አልነበረንም። ትኩረት አንሰጠውም ነበር'' ይላሉ።

በወጣትነታቸው ዘመን 'ፓርቲ' ተጋብዘው ከጓደኞቻቸው ጋር ታድመው ከነበሩበት ቤት በወላጆቻቸው ተይዘው መወሰዳቸውን ያስታውሳሉ። በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ ውስጥ ያለው አለመረጋጋት ድሬዳዋ ላይም ተፅዕኖ ማሳደሩን የሚናገሩት ወይዘሮ መሰሉ "ለአራት ቀናት ድሬዳዋ ፀጥታ ቢሰፍንም እኔ ግን ሴንት ቫለንታይንስ መከበሩ ጥሩ ነው እላለሁ። ከዚህም በተጨማሪ ከባለቤቱ ጋር የተፋታው ልጃቸውና ባለቤቱ እንዲሁም የልጅልጃቸው ቀኑንም በማሰብ ይገናኛሉ።

"ልጅና እናት ተለያይተው ቢኖሩም እንኳን በዓመት አንድ ቀን በዚህች ቀን ሰበብ ተገናኝተው እንዲተሳሰቡ ስላደረጋቸው ሴንት ቫለንታይን ጥሩ ጎን እንዳለው ይሰማኛል'' ብለዋል።

የ56 ዓመቷ የመቀሌ ነዋሪ ወይዘሮ ፀጋ በላይ በሰባዎቹ ከሚገኙት አቶ ተውሐሶም ገብሬ ጋር በትዳር ለ34 ዓመታት ኖረዋል። አቶ ተውሐሶም ስለ ቫለንታይንስ ቀን ቢያውቁም በተቃራኒው ወይዘሮ ፀጋ ሰምተው እንደማያውቁ ይናገራሉ። ወጣት በነበሩበት ወቅት እንዲህ አይነት በዓላት እንዳልነበሩም ይናገራሉ።

"ለፍቅረኞች የተመደበ ቀን ባይኖርም ደስተኛ ነበርን ምንም እንዲቀየርም አልፈልግም" ይላሉ ። ባለትዳሮቹ ፍቅር በየቀኑ መታወስ ያለበት ነገር መሆኑን በማስገንዘብ "ፍቅር በየቀኑ ክብር ሊሰጠው የሚገባ ነው። የዘመኑ ወጣቶች ፍቅርን በዚህ ቀን አስታውሰው ማክበራቸው ጥሩ ነው" ብለዋል።

Image copyright Getty Images

የዘመኑስ ልጆች ምን ይላሉ?

የ30 ዓመቷ ምስክር ታሪኩና የ33 ዓመቱ ሚካኤል ገብረ አምላክ በጓደኝነት በነበሩበት ወቅት እንዲሁም ከተጋቡም በኋላ የሴንት ቫለንታይንስን ቀን እንደሚያከብሩ ለቢቢሲ ገልፀዋል። ''ብዙ የተቀናጣ ሳይሆን በሆቴል ቤት አብረን በመመገብ፣ አበባ በመሰጣጣት አንዳችን ለአንዳችን ያለንን ፍቅር እንገልጻለን'' ትላለች።

በተጨማሪም ''እኔ የሴንት ቫለንታይንስን ቀን እወደዋለሁ ሆኖም ግን የሚዋደድ ሰው በየቀኑና ባገኘው አጋጣሚ ፍቅሩን መግለጽ መቻል አለበት'' በማለትም ትናገራለች።

በዓሉ ቁሳቁሶችንን ማሻሻጫ ምክንያት እንደሆነና በዓሉንም ከጓደኛዋ ጋር እንደማያከብሩ ስሟ እንዲጠቀስ ፈቃደኛ ያልሆነች ሴት ትናገራለች ''በበኩሌ ፍቅርን ለመግለጽ ፍቅረኛሞች በዚህች ቀን መወሰን አለባቸው ብዬ አላምንም። በዚያ ላይ ቁሳቁሶችን ለመሸጥና የሴቶችን ልብ ለማማለል ተብሎ የታሰበ በመሆኑ ሴንት ቫለንታይንስን ማክበር ደስ አይለኝም'' ትላለች።

በዓሉንም በተለየ መልኩ የሚያሳልፉትም አልታጡም ከእነዚህም ውስጥ አንዷ ምህረት እቁባይ አንዷ ናት። ከስድስት ዓመታት በፊት የተመሠረተውና በሴቶች መብት ዙሪያ የሚንቀሳቀሰው የ'የሎው ሙቭመንት' አባል የሆነችው ምህረት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎችንም ያግዛል። ከገጠር የሚመጡት አብዛኞቹ ተማሪዎች ገንዘብ እንደሚያጥራቸው የምትናገረው ምህረት በተለይም ሴት ተማሪዎች ለንፅህና መጠበቂያ ገንዘብ ስለማይኖራቸው ይቸገራሉ። ተማሪዎቹን ለመርዳትም አበባ በመሸጥ ገንዘብ ማሰባሰብ ጀመሩ። ወቅቱም ከዚሁ ቀን ጋር እንደተገጣጠመ ትናገራለች።

ከጊዜ በኃላ የተለያዩ የአበባ አምራቾች በየዓመቱ በነፃ አበባ ስለሚሰጧቸወም ብዙ ተማሪዎችን ለመርዳት ችለዋል። ምህረት እንደምትናገረው ባለፈው ዓመት 300 ሺህ ብር ገቢ አግኝተዋል።

''ሰዎች እርስ በእርሳቸው ጥሩ እንዲሆኑ ማበረታት የሚያስደስት ነገር ነው። ይህ ዕለትም በወንዶችና በሴቶች መካከል ያለውን ግንኙነት በፍቅር የሚያስተሳስር እንቅስቃሴ ስለሆነ የሚያስደስት ነው"በማለት ትገልጻለች።

Image copyright Getty Images

በቫለንታይስ ዙሪያ የተለያዩ የሥራ ዘርፎች ምን ይመስላሉ?

የተለያዩ ሬስቶራንቶችና ሆቴሎችም ዕለቱን ለማክበር ሽር ጉድ እያሉ ነው።

ለአራት ዓመታት ፖስታ ቤት አካባቢ በሚገኘው 'ጉስቶ ሬስቶራንት' በሥራ አስኪያጅነት የሠራው ሞገስ ቀለመወርቅ በዚህ ዕለትም ሬስቶራንቱ መግቢያ ላይ ፎቶግራፍ መነሳት፣ አበባ፣ ሻምፓኝና እንዲሁም የፍቅር ሙዚቃዎችን እንዳዘጋጁ ይናገራል። በተመሳሳይ መልኩ ሸራተን ከተከፈተበት ከሁለት አስርታት ዓመታት ጀምሮ ለዚህ በዓል ልዩ ዝግጅትም እንዳለቸው የሆቴሉ ማርኬቲንግ አስተባባሪ ሰላማዊት አዳነ ትናገራለች። ከሌሎች ቀኖች በተለየ መልኩ የተስተናጋጆች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የምትናገረው ሰላማዊት በዓመታትም ውስጥ የሚመጡት የኢትዮጵያውያን ቁጥር ጨምሯል ትላለች።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ክብረ-በዓሉ ትኩረት እያገኘ መጥቷል የምትለው ድምፃዊቷ ብሩክታዊት ጌታሁን (ቤቲ ጂ) ናት። በተለይም በሙዚቃው ዘርፍ ከሌሎች ቀናት በተለየ መልኩ ለዕለቱ የሚሆኑ ለስለስ ያሉ ዘፈኖችን ማጥናት እንደሚጠበቅባቸውም ትገልፃለች።

"ይህ የሃገራችን ባሕል ባይሆንም ማንነታችንና የእራሳችንን ባሕል እስካልረሳን ድረስ ብናከብረው ምንም ማለት አይደለም። በኔ አስተያየት ግን ፍቅር በአንድ ቀን ብቻ መከበር የለበትም። ቢሆንም ግን በተለይ ወንዶች ፍቅራቸውን እንዲገልጹ የሚያግዛቸው ከሆነ ጥሩ ነው" ትላለች።

በዛሬውም ዕለት የሙዚቃ ዝግጅቱን የሚያቀርበው ሙዚቀኛው ሳሙኤል ብርሀኑ (ሳሚ ዳን)ም የበዓሉ አከባበር እያደገ መምጣቱን ይገልፃል። በዚህ ዓመት ከሌላው ጊዜ በተለየ በጾም ላይ መዋሉ ሥራቸውን ሊያከብደው እንደሚችልም ያስባል።

"ያለፈውን የፍቅር ዓመት የሚያመዛዝኑበትና ለፊተኛው የፍቅር ዘመን ደግሞ የሚያቅዱበት የሚሆን ክብረ በዓል ቢሆን ጠቃሚ እንደሆነ ይሰማኛል። ስለ ፍቅር ማውራት ተገቢ ስለሆነ ሰው እንደየባሕሉ ቢያከብረው እመኛለሁ። ዕለቱ በተለይ እውነተኛ ፍቅር ላላቸውና ለመተጫጨት ላሰቡ ሰዎች ጥሩ ቀን ነው''ይላል።

Image copyright Neil Curry

በዚህ ዕለትም በአበባ እርሻ ላይ የተሰማሩ እርሻዎችም ሆኑ ድርጅቶች ሽያጫቸውም የሚጨምርበት ዕለት ነው። መናየ የአበባ እርሻ በዚህ ሥራ ከተሰማራ 11 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን እዚያ የምትሠራው ማሕደር ነጋሽ የዚህ ዕለት ሽያጫቸው የዓመቱን 75% ሽያጭ እንደሚያክል ትናገራለች።

በዕለቱም ቀይ ፅጌረዳዎች በጣም ተፈላጊነት አላቸው ትላለች።

"ቀይ ጽጌሬዳ ብዙ ሙቀትና ምቾትን የሚጠይቅ አበባ በመሆኑ በዚህ ዓመት ምርታችን በውርጩ ምክንያት ተጎድቷል። የእኛ ዋና ገዥዎች በኔዘርላንድ እንደመሆናቸው ከጅምራችን ለዚህ ቀን ያለን ገበያ በጣም ከፍ ያለ ነው'' ትላለች።

ከዚህም በተጨማሪ ለአንዳንድ የበጎ አድራጎት ማህበሮች በነፃ 2000 አበባዎችን ካለፉት 3ዓመታት ጀምሮ በየዓመቱ እያበረከቱ እንደሆነም ትናገራለች።

የዝግጅቶችና የዲኮር ባለሙያ የሆነቸው ሊና ከሊፋ ለሃያ ዓመታት ያህል የሠራች ሲሆን በዚህ ዕለትም ሥራዋ ምንም እንቅስቃሴ እንደሌለው ትናገራለች።

"የዛሬ 10 ዓመት አዲስ አበባ በዚህ ዕለት እንደዚህ አልነበረችም። ሰዎችን አገናኝቶ ለፍቅር ማሰባሰቡ ጥሩ ነው በዚያ ላይ ለፍቅረኛሞች በዓመት ውስጥ የሚደረግ አዲስና ለየት ያለ ነገር ይሰጣቸዋልና በጣም ደስ ይላል። እኔ ግን ዕለቱን አልወደውም ምክንያቱም ፍቅር በአንድ ቀን ሳይሆን በየዕለቱ መሆን አለት'' በማለት ትናገራለች።

እናንተስ ስለ ሴንት ቫለንታይንስ ምን ትሉናላችሁ? በፌስቡክ ገፃችን ሃሳባችሁን ያካፍሉን።

ተያያዥ ርዕሶች