"የመፍትሔ አካል ለመሆን በማሰብ በፍቃዴ ሥልጣኔን ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርቤያለሁ" ኃይለማርያም ደሳለኝ

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
"የመፍትሔ አካል ለመሆን በማሰብ በፍቃዴ ሥልጣኔን ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርቤያለሁ" ኃይለማርያም ደሳለኝ

ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከጠቅላይ ሚንስትርነታቸው እና ከኢህአዴግ ሊቀመንበርነታቸው ለመነሳት ጥያቄ አቅርበዋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ እንደዘገቡት ከሆነ፤ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከጠቅላይ ሚንስትርነታቸው እና ከኢህአዴግ ሊቀመንበርነታቸው ለመነሳት ጥያቄ አቅርበዋል።

በቀጣይ ጠቅላይ ሚንስትሩን ማን ሊተካ ይችላል የሚለው የበርካቶች ጥያቄ ነው።

ዛሬ ለተለያዩ ሚዲያዎችም በሰጡትም መግለጫ ሰሞኑን በኃገሪቱ ላይ በተከሰቱት አለመረጋጋቶች ምክንያት የብዙዎች ህይወት መጥፋት፣ከአካባቢያቸው መፈናቀል እንዲሁም ኢንቨስትመንቶች የተጓጎሉ መሆናቸውን ጠቅሰው ገዢው ፓርቲም ሆነ መንግሥት የተለያዩ ማሻሻያዎችንም እየሰራ ነው ብለዋል።

"ለነዚህ ማሻሻያዎች መሳካትም ሆነ እንዲሁም ላስቀመጥናቸው የመፍትሔ አቅጣጫዎች የመፍትሔ አካል ለመሆን በማሰብ በገዛ ፍላጎቴና ፍቃዴ የኢህአዴግ ኃላፊነቴንም ሆነ የመንግሥት ኃላፊነቴን ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርቤያለሁ" ብለዋል።

ጥያቄያቸውንም የደኢህዴን እንዲሁም የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መቀበላቸውን አመስግነዋል። "ሥልጣን መልቀቅ መፈለጌን በሰለጠነ መንገድ በአዎንታዊ ተቀብለውታል። " ብለዋል።

ጥያቄያቸው የመጨረሻ ውሳኔ የሚያገኘው በኢህአዴግ ምክር ቤት መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል። በቅርቡም የኢህአዴግ ምክር ቤት በሚያደርገው ስብሰባ ያቀረቡትም መልቀቂያ ተቀባይነት እንደሚያገኝ ተስፋ አድርገዋል።

ከስልጣን የመልቀቂያ ጥያቄያቸው ተቀባይነትም እስኪያገኝ ድረስ በተሰጣቸው ኃላፊነት እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

"የኢህአዴግ ምክር ቤት ፍፁም ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚተካኝን የኢህአዴግ ሊቀ-መንበር ይመርጣል ብየ አምናለሁ። በተመሳሳይ መንገድ ድርጅቱና መንግሥት ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በማድረግ በሀገራችን ዳግም ታሪክ የሚሰራበት ወቅት ነው ብየ አምናለሁ" ብለዋል።

ጨምረውም " እኔም በተራየ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየ የምጠራበት ሁኔታ ይፈጠራል ብየ እተማመናለሁ" በማለት የተናገሩት ኃይለማርያም ደሳለኝ ሀገሪቱ አሁን ያለችበት ሁኔታም እጅግ አሳሳቢም እንደሆነ ገልፀዋል።

"ይህንን አሳሳቢ ሁኔታ ለመቅረፍ መላው የአገራችን ህዝቦች ከዚህ በፊት የተለመደው ኢትዮጵያዊ የመቻቻል እና የመከባበር ሁኔታ እንዲቀጥል መስራት አለብን"ብለዋል።

ጨምረውም "በአገራችን ዋስትና እኔም በበኩሌ የድርሻየን ለማበርከት ዝግጁ ነኝ" ብለዋል።

የኢህአዴግ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ትናንት በሰጡት መግለጫ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በባለፉት ስድስት ዓመታት በሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲሁም በፓርቲው ሊቀ-መንበርነት ማገልገላቸውን አመስግነው ጥያቄያቸውም ተቀባይነት እንዳገኘ ገልፀዋል።

ጨምረውም የመጨረሻው ውሳኔ የኢህአዴግ ምክር ቤት እንደሚያፀድቀውና ምክር ቤቱም ካፀደቀው በኋላ በሀገሪቱ ህገ-መንግሥት መሰረት የፓርቲው ሊቀ-መንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ይሾማል ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሥልጣን የመልቀቅ ጥያቄም ተከትሎ የኢዴፓ ፓርቲ የቀድሞ መሪ አቶ ልደቱ አያሌው ሰሞኑን በቴሌቪዥን ከሚቀርቡ መከላከያ ሰራዊቱን የሚመለከቱ ዘገባዎች ተነስተው አንድ ነገር ሊኖር እንደሚችል ይጠረጥሩ እንደነበር ይናገራሉ።

" መንግስት የአመራር ክፍተት እንዳለበት መምራት እንዳልቻለ፣ ሕግና ስርአት ማስከበር እንዳልቻለ ግልፅ ነው።" ይላሉ።

የአቶ ኃይለማርያም ውሳኔ አገሪቱ ካለችበት ፖለቲካዊ አለመረጋጋት አንፃር የሚጠበቅ እና ተገቢ እንደሆነም አቶ ልደቱ ይገልፃሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢወርዱም እንኳን ስር ነቀል ለውጥ መምጣት ካልቻለ ብዙም ልዩነት እንደሌለው ይናገራሉ።

"ሌላ ሰው ቢተካ የአስተሳሰብ ለውጥ ካልመጣ አጠቃላይ የህዝብ ተቋማት ለውጥ መጥቶ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርአት መሸጋገር የሚያስችል ትክክለኛ የማሻሻያ እርምጃ ማድረግ ካልቻልን ዋጋ የለውም" ይላሉ።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ያልተረዳነው ነገር አለ የሚሉት አቶ ልደቱ የወታደሩ ሚና ምን እንደሚሆን እና የሲቪል አስተዳደሩ ይቀጥላል ወይስ ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ታውጆ ወታደሩ ወደ አመራር ይመጣል የሚለው ግልፅ እንዳልሆነም ይናገራሉ።

"ማሻሻያው ከኢህአዴግ እጅ ወጥቶ መንግስት በአዋጅ ማሻሻያ የሚሰራ ኮሚሽን ተቋቋሞ ድርድርም ከሌሎች ፖለቲካ ድርጅቶች ጋር መደረግ አለባቸው" ብለዋል።

በዚህ ደረጃ ኢህአዴግ ምን ያህል ተዘጋጅቷል የሚለው ግን ለአቶ ልደቱ ግልፅ አይደለም።

የታሪክ ምሁሩ አቶ አበባው አያሌው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው መረዳት የቻሉት የመፍትሔው አካል ለመሆን ስላልቻሉ ከሥልጣን ለመልቀቅ እንደወሰኑ ነው።

"በሐገሪቱ ያለውን ችግር ለመፍታት እና የተነሳውን ጥያቄ ለመመለስ በጎ እርምጃ ለመውሰድ ይህንን ውሳኔ እንደወሰኑ ከመግለጫቸው ማየት ችያለሁ" ብለዋል አቶ አበባው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ፖለቲካን በአግባቡ አያውቁትም እንዲሁም ከመጀመሪያው ወደ ስልጣን ሲመጡ በሙሉ ስልጣናቸው እንዳይሰሩ ለይስሙላ የተቀመጡ ነበሩ በሚል ብዙዎች አስተያየት ይሰጡ እንደነበር የሚናገሩት አቶ አበባው አሁን ያደረጉትንም ውሳኔ ደግፈዋል።

ያልቻለ ሰው መልቀቅ አለበት የሚሉት አቶ አበባው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ውሳኔያቸው ሊደነቁ ይገባል ብለዋል።

ተያያዥ ርዕሶች