በጎንደር የሥራ ማቆም አድማ እንደቀጠለ ነው

የአፄ ፋሲል ቤተ-መንግሥት

ብዙ ሁነቶችን ባስተናገደው ባለፈው ሳምንት ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና የመብት አቀንቃኞች በምህርትና በይቅርታ ተፈተዋል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው እንዲሁም ከፓርቲያቸው አመራር ኃላፊነት የመልቀቅ ጥያቄ ባቀረቡ ማግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ለብዙዎች አነጋጋሪ ሆኗል።

ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ በኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ ድንጋጌ በመንግሥታዊው ቴሌቪዥን በይፋ ከተገለፀበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ስሜቶች እየተስተናገዱ ሲሆን፤ በአንዳንድ የአማራ ክልል ከተሞች በአፀፋው የሥራ ማቆም አድማ አድርገዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በታወጀ 72 ሰዓታት ጊዜ ውስጥ በጎንደር ከተማ የስራ ማቆም አድማ የተነሳ ሰሆን የንግድ ቤቶች ተዘግተዋል እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ እንደተቋረጠ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልፀዋል። የጎንደር ከተማ ፀጥ ረጭ እንዳለችም ጨምረው ተናግረዋል።

በተቃራኒው የተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ክፍት እንደነበሩና አገልግሎትም ሲሰጡ እንደነበር ተነግሯል።

የኢፌዲሪ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት በፌስቡክ ገፁ ላይ እንዳሰፈረው ትናንት ምሽት የከተማው ከንቲባ አቶ ተቀባ ተባባል ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በከተማው ውስጥ የስራ ማቆም አድማ በተለይም የንግድ ቤቶችን መዘጋትና ትራንስፖርት ማቆም እንዳለ አምነው ነገር ግን "ህገወጥ ስለሆነ ህዝቡ ሊቃወመው ይገባል" ብለዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የጎንደር ነዋሪዎችም ግልፅ በሆነ ሁኔታ ማን አድማውን እንደጠራው አልታወቀም ብለዋል። የከተማው ከንቲባ በበኩላቸው "ባለቤቱ ያልታወቀ አድማ" ብለውታል።

"ህዝቡ በሰለጠነና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ጥያቄዎቹን አሁንም በማቅረብ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ተቀራርቦ መስራት አለበት" ቢሉም ከንቲባው በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ በሀገሪቱ ላይ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ ካልተነሳ በአድማው እንደሚቀጥሉ እየገለፁ ነው ።

ትናንት አመሻሹ ላይ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ከእስር የመፈታታቸውንም ዜና ተከትሎ በጎንደር ከተማ ደስታቸውን ለመግለፅ ብዙዎች እንደወጡ ነዋሪዎች ገልፀዋል።

በባህርዳር ከተማም ትናንት ጥዋት አካባቢ ላይ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የስራ ማቆም አድማ እንደነበርና የንግድ ቤቶችም መዘጋታቸውን ነዋሪዎች ገልፀዋል እንዲሁም በደብረ-ታቦር ከተማ መጠነኛ የሚባል የሥራ ማቆም አድማ እንደነበር መረዳት ተችሏል።

ሁለተኛ ቀኑን በያዘው በዚሁ የስራ ማቆም አድማ በጎንደር እንደቀጠለ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልፀዋል። የንግድ ቤቶች እንደተዘጉ ሲሆን የትራንስፖርት አገልግሎትም ዛሬም እንደሌለ እየተናገሩ ነው። ትናንት ክፍት የነበሩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች በዛሬው ዕለት አንዳንዶቹም ዝግ እንደሆኑ ነዋሪዎቹ ጨምረው ገልፀዋል።