"የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያስጨንቃቸው ጥቅማቸው የሚነካ ሲመስላቸው ብቻ ነው" ዶ/ር ታፈሰ ኦሊቃ

ተቃውሞ በኢትዮጵያ Image copyright STRINGER

በኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ ድንጋጌን ተከትሎ ከአሜሪካ ኤምባሲ ተቃዉሞ በተጨማሪ የአውሮፓ ሕብረት፣ ጀርመን፣ እንግሊዝ፣ ኔዘርላንድ እና ኖርዌይ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት የሐገሪቱ ጉዳይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ንግግር እና ድርድር እንዲያደርግ አሳስበዋል።

የአሜሪካ ኤምባሲና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ስላወጡት መግለጫ የኢትዮጵያ አቋም ምንድን ነው ለሚለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አቶ መለስ አለም ሲመልሱ "የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም የህብረተሰቡን ቅሬታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው። በህግ ጥላ ስር ቆይተው የተፈረደባቸውና ጉዳያቸው በሂደት ላይ የነበሩ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲ አባሎችን እንዲሁም አንዳንድ ግለሰቦችን ተለቀዋል። ሌሎችንም እርምጃዎችን እየወሰደ ባለበት ወቅት የተሰጠ መግለጫ በመሆኑ ጠቃሚም፣ ገንቢም አይደለም" ብለዋል።

መግለጫዎቹን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ በኋላ በሚወስዳቸው እርምጃዎች ላይ የሚያመጡት ለውጥ ይኖራል ወይ ተብለው የተጠየቁት አቶ መለስ " የለም፤ ምንም ለውጥ አያመጣም" በሚል አጠር አድርገው ነው የመለሱት።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፓለቲካል ሳይንስና የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት ዶክተር ታፈሰ ኦሊቃ በበኩላቸው፤ መግለጫዎቹ ከበፊቱ ጋር የሚሄድ አይደለም ከማለት በተጨማሪ በተቻላቸው መጠን በመንግሥት ላይ ጫና የመፍጠር ፍላጎትም እንዳላቸው ማሳያ ነው ብለዋል። ይሄ ጫናም "በሚሰጡት የኢኮኖሚ፣ ዲፕሎማሲና ሌሎች ድጋፎች ይገለፃል" ይላሉ።

አንድ ሀገር ብቻዋን ተነጥላ አትቆምም የሚሉት ዶክተር ታፈሰ "ከእኛ ጋር ባላቸው የግንኙነት ቅርበትና ርቀት እነዚህን ነገሮችን በሙሉ ሊጎዳ ይችላል የሚል ግምት ነው ያለኝ" ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሲያውጅ በችኮላ፤ በደረሰው ውጥረት ተጨናንቀው ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠው "እንዲህ ያለው የግብረ ኃይል መልስም ደግሞ ትክክለኛ በማይሆንበት ጊዜ ይህንን ነገር ቆም ብሎ መልሶ አይቶ እንዴት ጊዜውን ማሳጠር እንደሚችሉ ወይም ደግሞ ከናካቴው መሰረዝ እንደሚችሉ ሊያስቡበት ይገባል" በማለት ምሁሩ ይናገራሉ።

በተለይም የአሜሪካ ኤምባሲ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከማውገዝ ጋር ተያይዞ የአሜሪካና የኢትዮጵያ ግንኙነት እየተቀየረ ነው ወይስ ይቀየራል? በሚል ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ "የአሜሪካ መንግሥትም ይሁን የአውሮፓ መንግሥታት የሚያስጨንቃቸው የግላቸው ጉዳዮች እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገው አይደለም። የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያስጨንቃቸው የአርሱን ጥቅም የሚነካ መስሎ ሲታያቸው ብቻ ነው" ብለዋል።

ከሀገሮቹ ጥቅም አንፃር በተለይም ኢትዮጵያ ባላት ጂኦፖለቲካዊ (መልካ-ምድራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ) እንዲሁም ከፀረ-ሽብር ዘመቻ ጋር ተያይዞ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ቁርኝት ጠንካራ በመሆኑ፤ በሀገሪቱ አስከፊ ሁኔታ ቢፈጠር ወይም ጭልጥ ያለ ወታደራዊ ሥርዓት ቢመጣ ጥቅማቸው ስለሚነካ የከፋ ሁኔታ እንዲፈጠር እንደማይፈልጉና በዚህም ምክንያት የከፋ ሁኔታ እንዲፈጠር እንማይፈልጉ፤ ይህንንም እንደማይቀበሉት ዶክተር ታፈሰ ይገልፃሉ።