እስራኤል ካገር አልወጣም ያሉ ኤርትራውያን ስደተኞችን አሰረች

Israel flag

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ወደ ሩዋንዳ አንሄድም ያሉ 16 ኤርትራውያን ስደተኞች ለእስር ተዳረጉ።

የእስራኤል መንግሥት ስደተኞችን ካገር የማስወጣትንም እቅድ ተከትሎም ለእስር የበቁ የመጀመሪያዎቹ ስደተኞች ናቸው።

የእስራኤል መንግሥት በሀገሪቷ ተቀማጭነታቸውን ያደረጉ የኤርትራና የሱዳን ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳና ኡጋንዳ በመላክ ሙሉ በሙሉ ካገር የማስወጣት እቅድ አላት።

እስካሁን ባለው 600 የሚሆኑ ስደተኞች ከሀገር እንዲወጡ ትዕዛዝ የተሰጣቸው ሲሆን ወደ 35 ሺ የሚሆኑ ስደተኞችም ከሀገር የመባረር አደጋ ላይ እንደሆኑ አንድ የእስራኤል የስደተኞች መብት ድርጅት አስታውቋል።

ስደተኞቹ ሆሎት ከሚባለው የማቆያ ማዕከል የተወሰዱ ሲሆን በማእከሉም የረሀብ አድማ መነሳቱ ታውቋል።

የእስራኤል መንግሥት በጥር ወር አካባቢ ስደተኞቹ ካገር እንዲወጡ ቀነገደብ ያስቀመጠ ሲሆን ካለበለዚያ ግን እስር እንደሚጠብቃቸው ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር።

ስደተኞቹ እሰራኤልን በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ውስጥ ለቀው ለመውጣት ከተስማሙ 3500 ዶላር ይሰጣቸዋል ተብሏል።

በዚህ ወር መጀመሪያም የእስራኤል መንግሥት የቀድሞ የሰራዊት አባላት ኤርትራውያን ስደተኖችን ጥገኝነት እንደሚሰጥ ቃል ገብቶ ነበር።