በቦኮሀራም ጥቃት የጠፉ ሴት ተማሪዎች ተመለሱ

School girls

የፎቶው ባለመብት, Yobe State government

ሰኞ እለት በምዕራብ ናይጀሪያ ተከስቶ የነበረውን የቦኮ ሀራምን ጥቃት ተከትሎ ጠፍተው የነበሩ ሴት ተማሪዎች በሰራዊቱ እገዛ እንደዳኑ ባለስልጣናቱ ገልፀዋል።

ጥቃቱን ተከትሎ ወደ 100 የሚጠጉ ተማሪዎችና መምህራን ዳፓቺ በምትባለው ከተማ አካባቢ ወጣ ብሎ ወደሚገኝ ጫካ ሸሽተው ነበር።

የተማሪዎቹ ቤተሰቦች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ተማሪዎች በጭነት መኪና ተጉዘው ሲሄዱ አይተናል ብለው ነበር።

ይህ ጥቃትቦኮ ሀራም ቺቦክ ከተማ 270 ሴት ልጃገረዶችን ከትምህርት ቤት ከጠለፈ ከአራት አመት በኋላ የተከሰተ ነው።

የዮቤ ከተማ አስተዳደር በመግለጫቸውም እንደገለፁት ቁጥራቸው የማይታወቅ ልጃገረዶች "ከጠለፏቸው አሸባሪዎች" በሰራዊቱ እገዛ ሊድኑ ችለዋል ብለዋል።

የሮይተርስ ዜና ወኪል በበኩሉ ቤተሰቦችና የመንግሥት ባለስልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው ወደ 76 የሚሆኑ እንደተመለሱና አሁንም 13 የመሆኑት እንደጠፉ ነው።

በተጨማሪም ሮይተርስ ምክንያቱን ባይጠቅስም ሁለት ልጃገረዶች ሞተው እንደተገኙም ዘግቧል።

የዮቤ አስተዳደር ከዚህ ቀደም ልጃገረዶቹ ስለመጠለፋቸው ምንም አይነት መረጃ የለም ብለው ነበር።

ዳፓቺ ከቺቦክ በሰሜናዊ ምእራብ 275 ኪ.ሜ ርቀት የምትገኝ ከተማ ናት።

ኢስላማዊ አክራሪዎቹ ከተማዋ ከደረሱ በኋላ የተኩስ ሩምታ ከመክፈት በተጨማሪ ተቀጣጣይ መሳሪያዎችን ያፈነዱ ሲሆን ይሄም ሁኔታ ተማሪዎቹንና መምህራኖቹን ወደ ጫካ እንዲሸሹ አድርጓቸዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች የናይጀሪያ የፀጥታ ኃይል በጦር ጀት በመታጀብ ለጥቃቱ ምላሽ እንደሰጠ ተናግረዋል።

በትምህርት ቤቱ አቅራቢያ ያሉ የአካባቢዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት የሸሹት ብዙዎቹ ልጆች በአካበቢው በሚገኙ መንደሮች እንደተገኙና አንዳንዶቹም 30 ኪ.ሜ ርቀት እንደተጓዙም ተናግረዋል።

የዮቤ የፖሊስ ሚኒስትር እንደገለፁት ከ926 ተማሪዎች ውስጥ 815ቱ ወደ ትምህርት ቤት ተመልሰዋል።