"ሕገ-መንግሥቱ ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትርን በሚመለከት ክፍተት አለበት" ውብሸት ሙላት

Ethiopian Constitution

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄያቸውን ካቀረቡበት ማግሥት ጀምሮ እሳቸውን የሚተካቸው ማነው? ለሚለው ጥያቄ ብዙዎች ግምቶቻቸውን እየሰነዘሩ ነው።

አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በተለያዪ ምክንያቶች ከስልጣን በሚወርድበት ወቅት ስለ ተተኪው ግለሰብ ሕገ መንግሥቱ ምን ይላል? በሚል የህግ ምሁሩን አቶ ውብሸት ሙላትን ቢቢሲ ጠይቆ ነበር።

ሕገ መንግሥቱንም ጠቅሶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መሆን እንዳለባቸው ውብሸት ይናገራል።

የፓርላማ ሥርዓትን በሚከተሉ ሃገራት መካከል አሸናፊው የፖለቲካ ፓርቲ መንግሥት የሚመሰርት ሲሆን ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማፅደቁን ተግባር ያከናውናል።

በዚህም መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪነታቸው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመሆኑ የግድ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ሊሆኑ እንደሚገባም አቶ ውብሸት አፅንኦት ያስረዳል።

ሰሞኑን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እና በማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ በተደጋጋሚ ስማቸው እየተጠቀሰ ከሚገኙት ግለሰቦች መካከል አንዳንዶቹ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ካለመሆናቸው ጋር ተያይዞ ሌላ አማራጭ አለ ወይ ለሚለው ጥያቄ የህግ ባለሙያው ሲመልስ፤

"መንግሥት ካልፈረሰ፤ ተጠባባቂ ወይም የሽግግር መንግሥት እስካልተመሰረተ ድረስ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ያልሆነ ግለሰብ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ሊቀርብ አይችልም፤ ምክንያቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪነታቸው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለሆነ" ይላል።

ሌላው የህግ ባለሙያው አማራጭ ብሎ የሚያስቀምጠው የማሟያ ምርጫ ማድረግ ነው።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ያልሆነ ግለሰብ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆን ከተፈለገ ተቃዋሚዎችም ሆነ ሌሎች ግለሰቦች ተወዳድረው ምርጫውን ማሸነፍ የቻለ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆን እንደሚችል ውብሸት ይገልፃል።

ነገር ግን ይሄ ረዥም ጊዜ ሊወስድ እንደሚችልም ይናገራል።

ይህም ሆኖ ሕገ መንግሥቱ ክፍተት እንዳለው የሚናገረው አቶ ውብሸት፤ ይህንን ክፍተቱንም ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት በኋላ ትምህርት መውሰድ ይገባ እንደነበር ይገልፃል።

"እሳቸውም ሲሞቱ ተተኪያቸውን ሕገ-መንግሥቱ በግልፅ አላስቀመጠውም" ይላል።

ሕገ መንግሥቱ እንደሚያትተው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማይኖሩበት ጊዜ ተክተው ይሰራሉ እንዲሁም ተጠሪነታቸውም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው።

"በማይኖሩበት" ማለት በጊዜያዊነት፣ ለሥራ ጉብኝት በሚሄዱበት ወቅት፣ ቢታመሙ፣ እረፍት ላይ ቢሆኑ ማለት እንደሆነና ከስልጣን ቢለቁ፣ ቢባረሩ ወይም ቢሞቱ ማን ሊተካቸው ይችላል ለሚለው ሕገ-መንግሥቱ በግልፅ ባለማስቀመጡ ችግር እንደፈጠረም ጨምሮ ይናገራል።

"በየትኛውም ሃገር ጠቅላይ ሚኒስትር በሚለቅበት ጊዜ በጣም በአፋጣኝ መተካት አለበት፤ በአፋጣኝ ካልተተኩ ስልጣን ይገባናል የሚሉ በርካታ ተቀናቃኞች ሊፈጠሩ ስለሚችል ሃገሪቱን አደጋ ላይ ሊጥላት ይችላል ተብሎ ይታሰባል" ይላል።

በቀድሞው የነገሥታት ሥርዓት ወራሾችንም ያዘጋጁ እንደነበር የሚናገረው ውብሸት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት በኋላ ይህ ክፍተት መሞላት እንደነበረበትም ይናገራል።

በቅርብ ጊዜ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ አባይ ወልዱ በለቀቁበት ወቅት ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የክልሉ ምክር ቤት አባል ባይሆኑም የሟሟያ ወይም ሌላ ሙሉ ምርጫ እስከሚደረግ ድረስ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው የርዕሰ መስተዳድር ሥራ እንዲሰሩ ቢያደርጓቸውም ይህ ሁኔታ በፌዴራል መንግሥቱ መድገም ከባድ እንደሆነም ውብሸት ይገልፃል።

"ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ካልሆኑ ተጠሪነት ሊኖራቸው አይችልም፤ ምክር ቤቱም ሊቆጣጠራቸው አይችልም" የሚለው ውብሸት "ብዙ ምስቅልቅሎችን ያስከትላል" ይላል።

በአሜሪካ ጆርጂያ ጉኔት ኮሌጅ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት ዶክተር ዮሐንስ ገዳሙ በቀጣይ ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ሊሆን ይችላሉ? ለሚለውም ጥያቄም ሲመልሱ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ከብአዴን ወይም ከኦህዴድ ውስጥ በአመራር ላይ ያሉ አቶ ደመቀ መኮንን ወይም ዶክተር አቢይ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገምታሉ።

ዶክተር ዮሀንስ ኢህአዴግ እስካሁን እየሰራበት ያለውን አሰራር በማየትም አራቱ ፓርቲዎችም ሆነ መሪዎቻቸው የተለያዩ ቁልፍ የሚባሉ የስልጣን እርከኖችን ተከፋፍለው እንደሚጨብጡ ይናገራሉ።

''የፓርላማው አፈ-ጉባኤ ከኦህዴድ፣ ፕሬዚዳንቱ እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ናቸው'' የሚሉት ዶክተር ዮሀንስ ከዚያ አንፃር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከኦህዴድ ላይሆን ይችላል የሚል ግምት አላቸው።

"ይህ ሁኔታ ከተቀየረና ዶክተር አብይ ልዩ ዕድል የሚኖራቸው ከሆነ አመራሩ ላይ ያለው የስልጣን ክፍፍል ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ይቀያየራል"ይላሉ።

ያለውን ሁኔታ በማየትም ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ሊሆኑ እንደሚችሉ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

ተያያዥ ርዕሶች