ጎንደር፡ በአድማው ተሳትፈዋል የተባሉ ከሥራ ታግደዋል

የአፄ ፋሲል ቤተ-መንግሥት

ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ በጎንደር ከተማ ለሦስት ቀናት የቆየ የሥራ ማቆም አድማ ተጠርቶ እንደነበር ይታወሳል።

አድማው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመቃወም እንዲሁም የታሰሩ ይፈቱ የሚሉ አጀንዳዎችን አስመልክቶ የተካሄደ እንደነበርም ተዘግቧል።

በዚህ የሥራ ማቆም አድማ የተነሳ የንግድ ቤቶች ተዘግተው የነበረ ሲሆን የትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተቋርጦ የነበረ ሲሆን ከትናንትና ጀምሮ ግን አገልግሎቶች መጀመራቸውን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የጎንደር ነዋሪ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ነዋሪው እንዳሉት የትራንስፖርት አገልግሎት ባለመኖሩ ብዙዎች በእግራቸው ለመንቀሳቀስ ተገደው ነበር ብለዋል። ከአድማው ጋር በተያያዘ የትራንስፖርት አገልግሎት ያቋረጡ ተሽከርካሪዎች የሰሌዳ ቁጥራቸው እንደተወሰደ እንዲሁም የንግድ ቤቶችም እንደታሸጉ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

የጎንደር አጠቃላይ ሁኔታ ወደ ሰላማዊ ወደ ቀድሞው እንቅስቃሴ እንደተመለሰ የከተማው ከንቲባ አቶ ተቀባ ተባባል ገልፀው፤ የንግድ ቤቶች መታሸጋቸውንም የተሽከርካሪዎች የሰሌዳ ቁጥር እንደተወሰደ አረጋግጠዋል።

ይህም በጎንደር ከተማ የተከሰተው ሁኔታ የአስቸኳይ ጊዜ ከታወጀ በኋላ ከተከለከሉ ጉዳዮች አንዱ የሥራ ማቆም አድማ አንዱ መሆኑን ከንቲባው ይናገራሉ።

"በዚህም መሰረት አድማውን በመተባበር ይህንን ህግ የጣሱ የህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ የትራንስፖርት ተቋማት ተጠያቂ የሚሆኑበት እራሱን የቻለ ሥርዓት አለው። ለዚህም የሚያገለግል የተዘጋጀ የህግ ማዕቀፍም አለ" ብለዋል።

ይህ ቅጣት ተግባራዊ የሚሆነው ሁሉም ላይ እንዳልሆነ የገለፁት ከንቲባው፤ በተመረጡ የመንግሥት ቤቶችን ተከራይተው የንግድ እንቅስቃሴ በሚያከናውኑ ተቋማት እና በተመረጡ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ላይ እንደሆነ ይገልፃሉ። እነዚህ ተቋማት በአዋጁ መሰረት እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ከንቲባው ጨምረው ተናግረዋል።

እርምጃው የንግድ ቤቶቻቸውም የታሸጉባቸውን ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ለማስገባት የተወሰደ እርምጃ መሆኑንም አቶ ተቀባ ይናገራሉ።

እነዚህ የታሸጉ የንግድ ቤቶችም ይሁኑ የሰሌዳ ቁጥራቸው የተወሰደባቸው የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በምን ያህል ወቅት ወደ ሥራ ተመልሰው ይመለሳሉ ተብለው ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ከንቲባው አቶ ተቀባ ሲመልሱ "ትናንት እንዲመለስላቸው አቅጣጫ እንደተሰጠ" ገልፀዋል።

"የንግድ ተቋማትን በተመለከተ፤ የንግድ ህጉ የሚለው የቅጣት ሂደት ስላለ ሥራቸውን እየሰሩ ህጋዊ የሆነውን ሂደት ተከትሎ ክስ የሚቀርብበት ከዚያ ደግሞ ውሳኔ የሚሰጥበት ሁኔታ ይኖራል" ብለዋል።

በዚህ የሥራ ማቆም አድማ ብዙ ሰዎች እንደተስተጓጎሉ አቶ ተቀባ ገልፀው "ህዝቡ በሰለጠነና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ጥያቄዎቹን አሁንም በማቅረብ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ተቀራርቦ መስራት አለበት" ብለዋል።