''የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አሻሚ ቋንቋና ሰፊ ክልከላዎችን የያዘ ነው'' ሂዩማን ራይትስ ዋች

ሂዩማን ራይትስ ዋች

የፎቶው ባለመብት, Human Rights Watch

በቅርቡ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ቦታ የበለጠ ሊያጠበው እንደሚችል ሂዩማን ራይትስ ዋች ባወጣው ሪፖርት አስታወቀ።

ሪፖርቱ ጨምሮ እንዳለው መንግሥት በዓለም አቀፍ ሕጎች ጥበቃ የሚደረግላቸውን በነፃነት የመሰብሰብ፣ የመደራጀትና ሃሳብን የመግለፅ መብቶችን የሚከለክለውን ይህንን አዋጅ በአስቸኳይ እንዲያነሳ ወይም እንዲያሻሽል ጠይቋል።

ሪፖርቱ ቀደም ባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የፀጥታ ኃይሎች ከ20ሺህ በላይ ሰዎችን ማሰራቸውንና መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈፀሙን አስታውሷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ድንጋጌውን የሚተቹ የሚባሉ መረጃዎችን ማሰራጨት የሚከለክል ከመሆኑ በተጨማሪ የአዋጁን አፈፃፀም የሚከታተለው ኮማንድ ፖስት መገናኛ ብዙሃንን ለመዝጋት የሚያስችል ስልጣን ተሸጥቶታል።

ይህም በኢትዮጵያ ያሉት መገናኛ ብዙሃንና እየሰፋ የመጣውን የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ላይ አሳሳቢ ስጋት የሚደቅን ነው ብሏል ሪፖረቱ።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የሥልጣን መልቀቅ ጥያቄ በኋላ በመከላከያ ሚኒስትሩ ይፋ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አሻሚ ቋንቋና ሰፊ ክልከላዎችን የያዘ መሆኑን የገለፀው የሂዩማን ራይትስ ዋች ሪፖርት፤ ይህ ሁኔታ መንግሥት ለሚወስዳቸው ያልተገቡ እርምጃዎች አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል ብሏል።

አብዛኛዎቹ የመመሪያው ቋንቋዎች ግልፅ አይደሉም። በርካታ ቃላት ትርጉማቸው አልተቀመጠም።ለምሳሌ 'ከፀረ ሰላም ቡድኖች ጋር መገናኘት' ወይም 'መቻቻልንና አንድነትን የሚያውክ' ተግባርን ከመፈፀም መቆጠብ ይገኝበታል።

መንግሥት ሰላማዊ ጥያቄዎችን በሃይል በሚመልስበት የኢትዮጵያ ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ፤ እነዚህ ግልፅ ያልሆኑ አንቀፆች የፀጥታ ኃይሎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መጣስ ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን እንዳሻቸው እንዲወስኑ ገደብ የለሽ ስልጣን ይሰጣቸዋል ብሏል ሪፖርቱ።

ሌላው ችግር ያለበት የፀጥታ ሃይሎች አመፅን ለማስቆም ያልምንም ፍቃድ ትምህርትቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች እንዲገቡና እንዲያስሩ የሚፈቅደው አንቀፅ ነው።

ይህ አንቀፅ መኖሪያ ቤቶችን ያለምንም ፍቃድ እንዲፈትሹም ለፀጥታ ሃይሎች የሚፈቅድ ሲሆን ከቤት ያለመውጣት አድማን፣ንግድ ቤትን አለመክፈትን፣ መንገድ መዝጋትን ጨምሮ ሰላማዊ ተቃውሞን ይከለክላል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ሰው ያለ ኮማንድ ፖስቱ ትእዛዝ ሊታሰርና ሊከሰስ ይችላል። ተሃድሶ እንዲወስድም ይደረጋል። ክስ ሳይመሰረት በእስር ማቆየት የመብት ጥሰቶችና በፖለቲካ አመለካከት ማጥመቅ የሚስተዋልበት ነው። ስቃይና ያልተገባ እስረኛ አያያዝ በኢትዮጵያ ትልቅ ችግሮች ናቸው እንደሆነ ሂዩማን ራይትስ ዋች በሪፖርቱ አመልክቷል።