ሰሜን ኮሪያ ለሶሪያ የኬሚካል ጦር መሳረያ ማምረቻ ቁሶችን ታቀርባለች ተባለ

በኬሚካል ጦር መሳሪያ ጥቃት ከተጎዱ ሶሪያውያን አንዱ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ሰሜን ኮሪያ የኬሚካል ጦር መሳሪያዎችን ለማምረት የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን ለሶሪያ ትልክ እንደነበረ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሙያዎች ያገኙትን መረጃ በመጥቀስ በአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ተዘገበ።

ቁሳቁሶቹ አሲድን መቋቋም የሚችሉ የወለል ንጣፎች፣ ቱቦዎችና ተያያዥ እቃዎች እንደሆኑ ሪፖርቱ አመልክቷል።

ገና ይፋ ያልሆነው በእዚህ የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት ላይ እንደሰፈረው፤ የሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ባለሙያዎች በሶሪያ የጦር መሳሪያ ማምረቻ ተቋማት ውስጥ መታየታቸውን ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ዘግቧል።

ምንም እንኳን መንግሥት ቢያስተባብልም የሶሪያ ኃይሎች ክሎሪን የተባለውን መርዘኛ ጋዝ እየተጠቀሙ መሆናቸውን የሚያመለክቱ አዳዲስ ሪፖርቶች መውጣታቸውን ተከትሎ ነው ይህ መረጃ የወጣው።

በአሁኑ ጊዜ ሰሜን ኮሪያ በምታካሂደው የኑክሌር ፕሮግራም ምክንያት ዓለም አቀፍ ማዕቀብ ተጥሎባት ይገኛል።

ከሰሜን ኮሪያ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሶሪያ ተላኩ ከተባሉት ቁሳቁሶች መካከል ከፍተኛ ሙቀትና አሲድን የሚቋቋሙ የወለል ንጣፎችና ሌሎች ተያያዥ ቁሶች ናቸው። የወለል ንጣፎቹ የኬሚካል ጦር መሳሪያዎችን ለመስራት የሚያስችሉ ተቋማትን ለመገንባት እንደሚውሉ ተነግሯል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ አምስት ጊዜ በአንድ የቻይና የንግድ ተቋም በኩል ቁሳቁሶች ወደ ሶሪያ መላካቸውን ዎል ስትሪት ጆርናል ጋዜጣ ባወጣው ዘገባ አመልክቷል። እነዚህም በበርካታ ዓመታት ውስጥ ከተጓጓዙት ቁሶች መካከል የተወሰኑት እንደሆኑም ተገልጿል።

ሰሜን ኮሪያ ላቀረበቻቸው ቁሳቁሶች በተለያዩ ኩባንያዎች በኩል የሶሪያ መንግሥት ተቋም በሆነው የሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር ማዕከል አማካይነት ክፍያ እንደሚፈፀምላት ጋዜጣው ዘግቧል።