ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር. . .?

ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ሊሆን ይችላል?

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የስልጣን መልቀቅ ጥያቄያቸውን በይፋ ካቀረቡ አንድ ወር አለፋቸው።

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና በአንዳንድ የሃገሪቱ አካባቢዎች እየተከሰቱ ካሉት የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ጎን በበርካቶች ዘንድ በቀጣይ የኢህአዴግ ሊቀ-መንበርና የሃገሪቱ ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ይሆናል? የሚለው ጥያቄ አነጋጋሪ እንደሆነ ነው።

በዚህ ዙሪያ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) በአመራሩ ውስጥ ያደረገው ሽግሽግ በበርካቶች ዘንድ ዶ/ር አብይን ለቀጣዩ ቦታ የማመቻቸት እርምጃ እንደሆነ ተገምቷል።

የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄም (ብአዴን) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን አቶ ደመቀ መኮንን በድርጅቱ ሊቀ-መንበርነት እንዲቀጥሉ ወስኗል። ይህም ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ ሊወዳደሩ ይችላሉ የሚል ግምት እንዲኖር አድርጓል።

አቶ ኃይለማሪያም የመጡበት የኢህአዴግ አባል ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ቀሪውን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ዘመን የመጨረስ ድርሻ አለው በሚል እጩ ሊያቀርብ ይችላል እየተባለም ነው።

ደኢህዴን ባደረገው የአመራር ለውጥ በክልሉና በፌደራል መንግሥት ውስጥ የቆዩትን አቶ ሽፈራው ሽጉጤን በሊቀ-መንበርነት መምረጡን አሳውቋል። አቶ ሽፈራውም ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታው ከሚቀርቡት ውስጥ ሊሆኑ ይችላሉ ሲባል ይገመታል።

ከሁሉ ቀድሞ የአመራር ለውጥ በማድረግ ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤልን ሊቀ-መንበሩ ያደረገው ህዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ (ህወሐት) በብዙዎች ዘንድ ለጠቅላይ ሚኒስትርነቱ መንበር ፍላጎት እንደሌለው በግምት ደረጃ ይነገራል።

ነገር ግን እስካሁን ኢህአዴግ ማን ሊቀመንበሩና የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ አልሰጠም። አባል ብሔራዊ ድርጅቶችም እንዲሁ ሊቃነ-መናብርቶቻቸውን ከመሰየም ውጪ በይፋ የገለፁት ነገር የለም።

የህወሓት/ኢህአዴግ የቀድሞ አባልና በትግራይና በድርጅቱ ውስጥ በከፍተኛ የሃላፊነት ቦታ ላይ የነበሩት አቶ ገብሩ አስራት እንደሚሉት ሊቀ-መንበር የመምረጡ ነገር የሚወሰነው በአራቱ ድርጅት ውሳኔ መሰረት ነው።

አቶ ገብሩ እስካሁን ያለውን ዝንባሌ በመመልከት በዋናነት ሁለት እጩዎችን ''ከብአዴን አቶ ደመቀ መኮንንና ከኦህዴድ ዶ/ር አብይ አህመድ የቅርብ ተፎካካሪ ሆነው ይቀርባሉ'' ብለው ያስባሉ።

ለዚህም ''አቶ ደመቀ በሰላ ተተችተው ደክመዋል እስካልተባሉ ድረስ ምክትል በመሆናቸው የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ሊይዙ ይችላሉ'' በማለት ምክንያታቸውን ያስቀምጣሉ።

Image copyright EPRDF official

በሌላ በኩል ደግሞ ''በሃገሪቱ ውስጥ ባለው የፖለቲካ ሁኔታ ከኢህአዴግ አመራር ወጣ በማለት የኢትዮጵያንም ሆነ የሕዝቡን ጥያቄ እንመልሳለን ብሎ ከተነሳው ከኦህዴድ አመራር መካከል የሆኑት ዶ/ር አብይ ሌላኛው ተወዳዳሪ ይሆናሉ'' ብለው ያስባሉ አቶ ገብሩ።

በኢህአዴግ አሰራር የፓርቲውን ሊቀ-መንበር የሚሰይመው ምክር ቤቱ ነው። ምክር ቤቱ ከእያንዳንዱ ብሔራዊ ድርጅት በእኩል 45 ድምፅ የተወከሉበት 180 አባላት ያለው ነው።

ስለዚህም ሊቀ-መንበር ለመሆን አንድ እጩ ከሁለት አባል ድርጅቶች አባላት በላይ ድምፅ ማግኘት ይኖርበታል። እንደ አቶ ገብሩ ግምት ዶ/ር አብይና አቶ ደመቀ እጩ ሆነው ከቀረቡ ''በምርጫው ሂደት ተወዳዳሪዎቹ ከድርጅታቸው በተጨማሪ የህወሓትንና የደኢህዴን አባላት ድምፅን ማግኘት የግድ ይሆንባቸዋል።''

በዚህ የምርጫ ሂደት የኢህአዴግ ምክር ቤት አባላት ምርጫ ወሳኝ ነው። የምክር ቤቱ አባላት ካሉበት ብሔራዊ ድርጅት እጩዎች ውጪ በእራሳቸው ውሳኔ የፈለጉትን እጩ የመምረጥ ዕድል ቢኖራቸውም ይህ ሊሆን ይችላል በሚለው ላይ አቶ ገብሩ ጥርጣሬ አላቸው።

''በግልፅ ድምፅ የሚሰጥ ከሆነ አባላት በዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት አሰራር ስለሚያዙ ተመሳሳይ ምርጫ ሊያደርጉ ይችላሉ'' ሲሉ ያብራራሉ አቶ ገብሩ።

ጨምረውም ነገር ግን ብዙ ጊዜ እንደሚሆነው የድምፅ አሰጣጡ ምስጢራዊ ስለሚሆን የምክር ቤቱ አባላት ከራሳቸው ፓርቲ እጩና ከድርጅታቸው ፍላጎት ውጪ የመምረጥ እድል እንዳላቸው አመልክተዋል።

አቶ ገብሩ ለቀጣይ የኢህአዴግ ሊቀ-መንበርነትና ለሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት አቶ ደመቀ መኮንንና ዶ/ር አብይ አህመድ እጩ ሆነው እንደሚቀርቡ ያላቸውን ግምት ሲያስቀምጡ በሌሎቹ በኩል ያለውን ሁኔታም ገልፀዋል።

የቀድሞ ድርጅታቸው ህወሓትን በተመለከተ ዶ/ር ደብረፅዮን የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሆነው መሄዳቸው በውድድሩ ውስጥ እንዳይገቡ አድርጓቸው ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

ደኢህዴንን በተመለከተም ድርጅቱ በአቶ ኃይለማሪያም በኩል እድሉን ማግኘቱንና ''እስከማውቀው ተገምግመው ብቃት የላቸውም ተብለው በመውረዳቸው እንዲሁም እራሳቸውም አልፈልግም ብለው በመልቀቃቸው ይህ ዕድል ለእነሱ ተመልሶ የሚሰጥ አይመስለኝም'' ሲሉ ግላዊ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ማዕከላዊ ስብሰባ ተጠናቆ ወደ ምክር ቤት ስብሰባ ተሻግሯል። 180 አባላት ያሉት ምክር ቤት ከሚወያይባቸው አበይት አጀንዳዎች አንዱ የፓርቲውን ሊቀ-መንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያምን የሚተካ መሪ መምረጥ ነው። ከሚቀጥሉት ቀናት በአንዱም ገዢውን ፓርቲና ሃገሪቱን የሚመራ ግለሰብ ሊታወቅ እንደሚችል ይጠበቃል።

ተያያዥ ርዕሶች