''ከ122 ዓመት በፊት የተጣለ መሰረት ዛሬ እየተናደ እንዳይሆን'' ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ

ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ

የታሪክ ምሁርና የግጭቶች ተመራማሪው ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ፤ የዛሬ 122 ዓመት ዓድዋ ላይ የተጣለ መሰረት ዛሬ እየተናደ እንዳይሆን ስጋት አላቸው።

ዛሬም የሃገሪቷን አንድነት የሚያሰጋ ሁኔታ ላይ ያለንበት ምክንያት "ያልሰራነው የቤት ሥራ ምን ይሆን?" ሲሉም ይጠይቃሉ። "ዛሬ ስለ ኢትያጵያዊነት እና ስለ ብሔረ-መንግሥት መነጋገራችን አሳዛኝ ነው" ይላሉ።

"ገዢው ፓርቲ ዲሞክራሲንና ነፃነትን ጨምድዶ ይዞ ቦታውን ለፅንፈኞች ስላመቻቸ ሃገሪቱን አደጋ ላይ ጥሏታል" የሚሉት ፕሮፌሰር ገብሩ ከውስጥም ከውጭም "ጠንቀኛ ፖለቲካ የሚያራምዱ" እንዳሉም ጠቅሰዋል።

ያልተተገበረ ህገ- መንግሥት

ፕሮፌሰር ገብሩ ሦስት መንግሥታትና ሦስት ህገ-መንግሥታትን ያሳለፉ ናቸው። በመርህ ደረጃ አሁን ሥራ ላይ ያለው ህገ-መንግሥትና ፌደራላዊ ሥርዓት የተሻለ መሆኑን ይናገራሉ::

ይሁን እንጂ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ አቀረቡት ባሉት መሰረት መሻሻል እንዳለበትም ያምናሉ።

እሳቸው እንደሚሉት የኢፌዴሪ ህገ-መንግሥት በመሰረቱ ጥሩ ይሁን እንጂ ተግባራዊነቱ ጥያቄ ውስጥ ይገባል። ለምሳሌ ህገ- መንግሥቱ ለክልሎችና ለፌደራል መንግሥት ያስቀመጠው የስልጣንና የሃብት ክፍፍል ተጥሶ እንደቆየ በዋናነንት ያነሳሉ።

በተለይ የ1993 ዓ.ም የህወሓት ክፍፍልን ተከትሎ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ስልጣንን ለብቻቸው ጠቅልለው ስለያዙት፤ የክልሎች መብትና ስልጣን ተቀንሶና ተንዶ ቆይቷል ይላሉ።

በ2008 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው አመፅ በአንድ ግዜ የተከሰተ እንዳልሆነ የሚጠቅሱት ፕሮፌሰር ገብሩ፤ የህገ- መንግሥቱ አለመተግበር፣ የአንድ ፓርቲ ጠቅላይነት፣ ህዝቡ መብቶቹን ለማስጠበቅ መንገዱ እየጠበበ መምጣት እንዲሁም ብሶቱን በአደባባይ የሚያሰማበት መንገድ መዘጋቱ እንደ መነሻ ይጠቅሳሉ።

ፕሮፌሰር ገብሩ በትምህርቱ ጥራት ላይ ጥያቄ ቢያነሱም፤ ባለፉት 27 ዓመታት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መስፋፋታቸውን ያደንቃሉ። ይሁን እንጂ "በየዓመቱ በሺዎች ቢመረቁም ኢኮኖሚው ግን ይህን የሚሸከመው አልቻለም። ስለዚህም ሥራ አጥነት በዚሁ ልክ ጨምሯል" ይላሉ።

እነዚህ ሁኔታዎች የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ራሱን እንዲመረምር ገፋፍቶታል የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ እነለማ መገርሳ 'ፖፕሊስት' (የህዝቡን የልብ ትርታ የተረዱ) መሪዎች ይሉዋቸዋል። የህዝቡንም ችግር ለመፍታት ሞክረዋል ይላሉ።

የምስሉ መግለጫ,

ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ

የፍርሃት እርምጃ

ኣራቱ የኢህአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶችንም "ራሳችንን ፈትሽናል ወቅታዊና ጊዜያዊ መፍትሄ እንሰጣለን" ብለው ደጋግመው ቢማፀኑም "ህዝቡ በዚህ አልረካም" ይላሉ።

በግንባሩ እርምጃዎች ህዝቡ አለመርካቱን አመላካች ያሉት፤ አሁን በድጋሚ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ምክንያት መፈጠሩን ነው።

"አዋጁ አስገራሚ ነው፤ ከፍርሃት የመነጨ ይምስለኛል" የሚሉት ፕሮፌሰር ገብሩ፤ ለችግሩ መሰረታዊ መፍትሄ እንደማይሆን ይሞግታሉ።

በቀጥታ ከህዝቡ፣ ከተቃዋሚዎች፣ ከምሁራን እና ከፖለቲካ ጠበብት ጋር መመካከርንም በመፍትሄነት ያስቀምጣሉ።

"መፍትሄው ሁሉን አቀፍ መሆን አለበት። ህዝቡ በአገሩ ጉዳይ ላይ ሊነጋገር ይገባል። ህግም ቢወጣ የሚተገብረው ህዝቡ ነው። ታንክና የጦር መሳርያ ማሰለፍ ሁኔታውን አይቀይረውም" ይላሉ ለጊዜው ፋታ ይሰጥ እንደሆነ በመገመት።

"አሁን የደረስንበት የሃገርን አንድነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ችግርን ኢህአዴግ ብቻውን የሚወጣው አይደለም" ይላሉ ጨምረው።

ፓርላማው በኢህአዴግ 'ካድሬዎች' ብቻ መሞላቱና የፍትህ አካሉ የለም በሚባልበት ደረጃ መድረሱን የሚናገሩት ፕሮፌሰር ገብሩ፤ "ተወቃሹ ሥራ አስፈፃሚው ብቻ ሳይሆን ግንባሩ በአጠቃላይ ነው" ይላሉ። በገዢው ፓርቲ የሥራ አስፈፃሚው ጉድለት ነው ተብሎ የሚቀርበውን በመቃወም።

ያለተጠያቂነትና ያለግልፅነት ሃገሪቱን ለ27 ዓመታት የመራ ድርጅት በማለት ግንባሩን ነቅፈው፤ "በድርጅቶች መካከል ያለው አለመተማመን አንድ ገዢ ፓርቲ ያመጣው አበሳ ነው" ይላሉ።