የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተቃውሞ ቢገጥመውም በምክር ቤቱ ፀደቀ

የመንግሥት አርማ

የካቲት 09/2010 ዓ.ም ቀን በመላው ሃገሪቱ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀደቀ።

ከእረፍት ተጠርቶ አስቸኳይ ስብሰባ ያደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ለስድስት ወራት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፅድቋል።

መጀመሪያ ላይ አዋጁ 346 የምክር ቤት አባላትን ድጋፍ እንዳገኘና 88ቱ ደግሞ የተቃውሞ ድምፅ እንደሰጡ እንዲሁም የሰባት አባላት ድምፅ በታዕቅቦ መመዝገቡ ቢገለፅም ከሰዓታት በኋላ ከምክር ቤቱ የወጣ መረጃ የተገኘው የድጋፍ ድምፅ ከፍ እንደሚል ገልጿል።

አቶ ያቆብ ወልደሰማያት የምክር ቤቱ ሕዝብ ግኑኘነት እንዳሉት ''በቆጠራ ላይ በተከሰተ ስህተት እንጂ የደገፉት ሰዎች ቁጥር 395 ነው'' ብለዋል።

ነገር ግን ስህተቱ እንዴት ሊፈጠር እንደቻለ ሊያስረዱ አልቻሉም።

የአዋጁን መደንገግ ከተቃወሙት መካከል አብዛኛዎቹ የኦህዴድ አባላት እንደሆኑ ተነግሯል።

ለሁለተኛ ጊዜ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ ሕገ-መንግስቱንና ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን ከአደጋ ለመጠበቅ መታወጁን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ አመልክቷል።

ምክር ቤቱ ከአባላቱና ከሕግ ባለሙያዎች የተወጣጡ ሰባት አባላት ያሉት ቦርድ ይቋቋማል ብሏል።

ቦርዱ ካሉት ሥልጣንና ኃላፊነቶች መካከል፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት የታሰሩትን ግለሰቦችን ስም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይፋ ማድረግና የታሰሩበትን ምክንያት መግለፅ ይገኝበታል።

ከዚህ በተጨማሪም ማናቸውም የሚወሰዱ እርምጃዎች ኢሰብዓዊ አለመሆናቸውን እንደሚቆጣጠር፤ ኢሰብዓዊ ሆነው ከተገኙ ደግሞ ፈጻሚዎቹን ለፍርድ እንዲቀርቡ ያደርጋል ተብሏል።

የአሜሪካን መንግሥትን ጨምሮ በርካታ ምዕራባውያን ሃገራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መተቸታቸው የሚታወስ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ተቃዋሚዎች እና የመብት ተሟጋቾች በተለያየ መልኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አዋጁን እንዳይደግፉ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ተያያዥ ርዕሶች