አይ ኤስ በኒጀር የአሜሪካ ወታደሮችን ሞት የሚያሳየውን ተንቀሳቃሽ ምስል ለቀቀ

የትዳር አጋሯን በጥቃቱ ያጠዓች አሜሪካዊት ባሏን ስትሰናበት Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ የትዳር አጋሯን በጥቃቱ ያጣች አሜሪካዊት ባሏን ስትሰናበት

አይ ኤስ እስላማዊ ቡድን ባለፈው ጥቅምት ወር በኒጀር በተሰማሩ የአሜሪካ ፀረ ሽብር ግብረ ሃይል ወታደሮች ላይ በፈጸመው ጥቃት የተገደሉ ወታደሮችን የሚያሳይ ተንቀሳቃሸ ምስል ይፋ አደረገ።

ተንቀሳቃሽ ምስሉ በእስላማዊ ቡድኑ የመልእክት መቀባበያ ላይ እስካሁን ሳይለቀቅ ለምን እንደዘገየ ግልፅ አይደለም።

ተንቀሳቃሽ ምስሉ ከወታደሮቹ በአንዱ የጭንቅላት ቆብ ላይ በተገጠመ ካሜራ የተቀረፀ ነው።

ጥቃቱ በኒጀር በሚገኙ የአሜሪካ ፀረ ሽብር ግብረ ሃይል ወታደሮች ላይ በእስላማዊ ቡድኑ መፈፀሙን ለመግለፅ የታለመ ይመስላል።

ተንቀሳቃሽ ምስሉ ሲጀምር ለእስላማዊ ቡድኑ መሪ አቡ ባክር አል ባግዳዲ ያላቸውን ታማኝነት በሚያሳዩ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያላቸው ቡድኖችን ያሳያል።

ባለፈው ወር በተለያዩ ተንታኞች ይህ ግንኙነት የተገመተ ቢሆንም በእስላማዊ ቡድኑ በሚጠቀምባቸው የመገናኛ ብዙሃን ግን በይፋ እስካሁን ድረስ አልቀረበም ነበር።

ከሞቱት ወታደሮች የአንዱ ወታደር ባለቤት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለማጽናናት በስልክ ባነገሯት ወቅት በተናገሩት ነገር በማዘኗ ውዝግብ መፈጠሩ ይታወሳል።

ተንቀሳቃሸ ምስሉ በርካታ ወታደሮች በበረሃ ውስጥ ምሽግ ለመያዝ ሲሮጡ ያሳያል ሲል ቢቢሲ ሞኒተሪንግ ዘግቧል ።

በተንቀሻቃሽ ምስሉ ላይ ወታደሮች ሲታኮሱ እንዲሁም የሞተ ወታደር ምስል ይታይበታል።

ተንቀሳቃሽ ምስሉን የቀረፀው ወታደር እስኪገደል ድረስ ውጊያው ቀጥሎ እንደነበር ከቪዲዮው መረዳት ይቻላል።