የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጉዳይ መንግሥትን እከሳለሁ አለ

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ አርማ Image copyright Facebook/OFC

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ (ኦፌኮ) በቅርቡ የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀበት መንገድ ህጋዊነት የጎደለው በመሆኑ መንግስትን ሊከስ እየተዘጋጀ እንደሆነ አስታወቀ።

የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት የቆየ ስብሰባ ካደረገ በኋላ ባወጣው የአቋም መግለጫ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንደሚቃወም ገልጿል።

የኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ በቀለ ገርባ ለቢቢሲ እንደገለፁት ፓርቲያቸው አዋጁን አስፈላጊ የሚያደርግ ነባራዊ ሁኔታ አለ ብሎ አያምንም።

ከዚህም ባለፈ አዋጁ በሕዝብ ተዋካዮች ምክር ቤት የፀደቀበት አግባብ ህጋዊነት እንደሚጎድለው ፓርቲያቸው ስለሚያምን ጠበቃ አቁሞ መንግስት ወደችሎት ሊወስድ ተሰናድቷል።

አዋጁ የፀደቀበት ሒደት የቁጥር ስህተት ያለበት፥ ይህንንም በመገንዘብ አባላቱ ከወጡ በኋላ የተሰጠው ድምፅ ሁለት ሶስተኛ እንደማይሞላ በመረዳት ማስተካከያ የተደረገበት፥ ሁለት እጃቸውን ያወጡ አባላት የተስተዋሉበትም ጭምር ነው ሲል ኦፌኮ በመግለጫው ነቀፌታውን አቅርቧል።

"የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታወጀበትም የፀደቀበትም አካሄድ ህገ መንግስቱን የሚጥስ እና በህግም የሚያስጠይቅ ነው። እኛ አሁንም አገሪቷ በህግ ነው የምትመራው ብለን ስለምናምን ጠበቃ ቀጥረን ጉዳዩን ወደፍርድ ቤት እንወስዳለን" ሲሉ አቶ በቀለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ