ደቡብ አፍሪካዊው አትሌት በዘራፊዎች እግሩ ሊቆረጥ ነበር

ደቡብ አፍሪካዊ አትሌት ምህሊንጊ ግዋላ

ደቡብ አፍሪካዊው አትሌት፣ ግዋላ ዘራፊዎች እግሩን በመጋዝ ሊቆርጡት እንደነበር ጓደኛው ለቢቢሲ ተናገረ።

አትሌቱ ጥቃቱ ሲደርስበት የድረሱልኝ ጩኸት ያሰማ ቢሆንም ማንም የሰማው አልነበረም።

እንደ ጓደኛው ሳንዲል ሻንጌ ከሆነ ጥቃቱን ያደረሱት ግለሰቦች ሶስት ሲሆኑ እግሩ ሙሉ በሙሉ ከመቆረጥ የዳነው አጥንቱ ላይ ሲደርሱ በመተዋቸው ነበር።

ዘራፊዎቹ የአትሌቱን ስልክ፣ ሰአቱንም ሆነ ብስክሌቱን ያልወሰዱ ሲሆን ዝም ብለው ከመንገድ ዳር በማውጣት ጥቃት እንዳደረሱበት ጓደኛው አስረድቷል።

"ለእርዳታ እየጮኸ የነበረ ቢሆንም በጣም ማለዳ ስለሆነ ማንም ሊሰማው አልቻለም ብሏል።"

አትሌቱ መጋዙ በአንደኛው እግሩ ላይ ሲቀረቀር እና አጥቂዎቹ ወደዛኛው እግር ሊሸጋገሩ ሲሉ የነበረችውን አጋጣሚ በመጠቀም አመለጠ።

ገፍተሯቸው እንደምንም ወደ ዋናው መንገድ ከገባ በኋላ መንገደኛ አግኝቶት ደርባን ወዳለው ሆስፒታል ተወሰደ።

ዶክተሮች እግሩን ሊድን እንደሚችል የተናገሩ ሲሆን እንደቀድሞው ቆሞ መሄድ እስኪችል ግን ረዥም ጊዜ እንደሚፈጅበት ተናግረዋል።

ጥቃቱ ለምን እንደደረሰበት ግልጽ ባይሆንም ምርምራው ግን አሁንም እንደቀጠለ ነው።

ተያያዥ ርዕሶች