የኬንያው ፕሬዝዳንት ከተቃዋሚው ራይላ ኦዲንጋ ጋር እርቅ ለማድረግ ተስማሙ

ፕሬዝዳንት ኬኒያታ (በስተግራ) የተቃዋሚውን መሪ ራይላ ኦዲንጋን (በቀኝ በኩል) በሃራምቤ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ በጋራ ከሰጡ በኋላ ሲጨብጡ Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ራይላ ኦዲንጋ (በቀኝ በኩል) ኡሁሩ ኬኒያታን (በስተግራ በኩል) እንደ ፕሬዛዳንት ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው ነበር

የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታና ተቃዋሚው ራይላ ኦዲንጋ እርቅ ለማድረግ ተስማሙ።

ያለፈውን ምርጫ ተከትሎ ሁለቱ ተቀናቃኞች ከባድ ፍጥጫ ውስጥ ገብተው የነበረ ሲሆን ከምርጫው በኋላ በተፈጠረው አለመረጋጋት 150 ሰዎች ሞተዋል።

ካለፈው ምርጫ ውዝግብ በኋላ ባላንጣዎቹ በይፋ ውይይት ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያቸው ነው። ኡሁሩና ራይላ ከተወያዩ በኋላ በቀጣይ ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት ቃል ገብተዋል።

ከጥቂት ወራት በፊት በአገሪቱ የተደረገውን ምርጫ ውጤትን ያልተቀበሉት ራይላ ራሳቸውን የህዝብ ፕሬዝዳንት ብለው በመሾም በዓለ-ሲመት ፈፅመው ነበር።

እስከ ዛሬ ሁለቱም ተቀናቃኞች ለውይይት ሲቀርብላቸው የነበረን ጥሪ ውድቅ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በጋራ በሰጡት መግለጫ ኡሁሩ ኦዲንጋ እንደ ወንድማቸው እንደሆኑ በመጥቀስ "በመካከላችን ለምን ችግር እንደተፈጠረና እንደከፋፈለን እንነጋገራለን"ብለዋል።

ኦዲንጋ ደግሞ በበኩላቸው "ልዩነታችንን የምንፈታበት ጊዜ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።