ጤፍ ሃገሩ የት ነው? ደቡብ አፍሪካ? አውስትራሊያ? . . .

አዲሲኒያ Image copyright RUTH LISHANU

ፈረንሳይ የምትኖረው የ28 ዓመቷ አትዮጵያዊት ሩት ሊሻኑ በንግድ ሥራ እራሷን ካቋቋመች 3 ዓመታትን አስቆጥራለች፤ የተሰማራችውም ከአፍሪካ የሚመጡ የተለያዩ ምርቶችን በማከፋፈል ነው። ሩት ለገበያ ከምታቀርባቸው ምርቶች መካከል ጤፍ እንዱ ነው።

ሩት ወደ ፈረንሳይ የሄደችው የዛሬ 10 ዓመት ነበር። አካሄዷም ለትምህርት ሲሆን በትምህርቷ ገፍታ ሁለተኛ ዲግሪዋን በንግድ ሥራ ለመያዝ በቅታለች። በትምህርቷ ማጠናቀቂያ ላይ ለመመረቂያ የሚሆን በንግድ ሃሳብ ላይ የሚያተኩር ወረቀት ማቅረብ ነበረባት። ይህም አሁን የተሰማራችበትን ሥራ እንድትጀምር ጠቅሟታል።

የዛሬ አራት ዓመትም ሩት በምን ዓይነት የንግድ ሥራ መሰማራት እንደምትችል ማጥናት ጀመረች። በዚያን ጊዜ ለጤና ተስማሚ እንደሆኑ የሚነገርላቸው 'ግሉተን' የተባለው ይዘት የሌላቸው ምግቦች በጣም ተፈላጊነት ነበራቸው። ጤፍ ደግሞ ከእነዚህ ምርቶች መካከል ቀዳሚው ነው።

በዓለም ዙሪያ ታዋቂ ከሆኑት ሰዎች መካከልም እንደእነ ቪክቶሪያ ቤክሃም ያሉ ሰዎችም የጤፍን ጠቀሜታና ከ'ግሉተን' ነፃ መሆኑን የመሰከሩበት ጊዜ በመሆኑ ትኩረቷን ወደምታውቀው የሃገሯ ምርት ጤፍ አዞረች።

በዚህ መልኩ የጤፍ ገበያውን አዋጪነት የተረዳችው ሩት ጤፍና የጤፍ ምርቶች ላይ ትኩረቷን ማድረግ ጀመረች። እግረ መንገዷንም ሌሎች ምርቶችን በንግድ ሃሳቧ ላይ አካተተች።

Image copyright RUTH LISHANU
አጭር የምስል መግለጫ ሩት የኢትዮጵያን ጤፍ ወደ ፈረንሳይ ለማስመጣት የንግድ ሃሳቧን ስታቀርብ

ሩት የገበያ ጥናት ባካሄደችበት ጊዜ በአዋጪነቱ ላይ ብቻ ሳይሆን የበርካቶችን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ ለጤና ተስማሚ የሆኑ ምርቶች ለማቅረብ ወሰነች። ከኢትዮጵያ በተጨማሪም ከደቡብ አፍሪካ፣ ከናይጄሪያና ከሌሎችም ሃገራት የተወጣጡ መሰል ምርቶችን ወደ ፈረንሳይ አስመጥቶ ለገበያ ማቅረብ ጀመረች።

ባለችበት ሃገር የጤፍን ጠቃሚነት ለማስረገጥ ጊዜ ፈጅቶባት እንደነበር ሩት ትናገራለች። በወቅቱ ፈረንሳይ ውስጥ ጤፍ ብዙም ባለመታወቁ ''በላቦራቶሪ ተገቢው ምርመራ ተደርጎበት ተፈላጊዎቹ የምግብ ንጥረ-ነገሮች እንዳለውና ለጤና ጠቃሚ መሆኑን ማረጋገጫ ማቅረብ ነበረብኝ'' ትላለች።

በተለያዩ ባለሙያዎች በጤፍ ላይ የተደረጉት ጥናቶች ለጤና ተስማሚ እንደሆነ ከማረጋገጥ ባሻገር ጤፍን 'ሱፐርፉድ' ወይም 'ልዕለ-ምግብ' የሚል ስያሜ እሰጥቶት እውቅና እንዲያገኝ አድርገዋል።

''ይህ ውጤት ከተገኘ በኋላም ጤፍን የበለጠ ለማወቅ በምርቱ ላይ የሚካሄደው ጥናትም ሆነ ምርምሩ አላበቃም'' ትላለች ሩት።

የሥነ-ምግብ ባለሙያዎች ባደረጉት ጥናት ጤፍ ባለው ይዘት መሠረት በሚያስገርም ሁኔታ የተለያዩ የጤና ጥቅሞች እንዳሉት ተረጋግጧል። የተለያዩ ቫይታሚኖች፣ ፕሮቲን እና ሌሎችም ይዘቶች ስላለው በተለይ ለስፖርተኞች 'አይረን' የተሰኘው ንጥረ-ነገር በኃይል ሰጪነቱ ተፈላጊ ነው።

በተጨማሪም በፈረንሳይ ውስጥ ሥጋን የማይመገቡ በርካታ ሰዎች ስላሉና ከሥጋ ያገኙ የነበረውን ለጤንነታቸው አስፈላጊ የሆነውን 'ቫይታሚን ቢ'ን ለማሟላት ከሩዝና ከበቆሎ በተሻለ የጤፍ ምርትን ይመርጣሉ ይህ ደግሞ የጤፍን ተፈላጊነት እንዲጨምር አደረገው።

''እኔ ጤፍን የማውቀው በእንጀራ መልኩ ብቻ ነበር። ነገር ግን ከእንጀራ ባሻገር የጤፍ ዱቄት በምን ዓይነት መልክ ለምግብነት ሊቀርብ እንደሚችል መሞከርና ማወቅ ነበረብኝ'' ትላለች ሩት።

Image copyright RUTH LISHANU
አጭር የምስል መግለጫ በጤፍ የተሠራ ዳቦ

ሩት ሊሻኑ ነዋሪነቷን ያደረገችው ሊዮ በምትባለው የፈረንሳይ ከተማ ነው። ሊዮ ደግሞ የሃገሪቱ የምግብ ከተማ በመባል ትታወቃለች። በዚህች ከተማ በጣም ታዋቂ የሆኑ ምግብ ቤቶችና የምግብ ባለሙያዎች (ሼፎች) አሉ። ከእነዚህም መካከል 'ቦኩስ' የሚባለው በጣም ታዋቂው ምግብ ቤት በከተማዋ ይገኛል።

እዚያ ከሚገኙት የምግብ ባለሙያዎች ጋር ተነጋግራ በጤፉ ዱቄት የተለያዩ ምን ዓይነት የምግቦች ሊዘጋጁ እንደሚችሉ አሠራሩን በሙከራ እንዲያረጋግጡ ሰጠቻቸው።

ባለሙያዎቹም ከሃገሬው የምግብ ልምድ ጋር አብረው ሊሄዱ በሚችል መልኩ በፓስታ፣ በፓንኬክና በኬክ ውስጥ እንደ ዋነኛ ግብዓት ሆኖ በተለያየ መንገድ ለየት ያሉ የምግብ ዓይነቶችን ሠርተው ማረጋገጥ ቻሉ።

በተጨማሪም ባለሙያዎቹ ጤፍ ከእንጀራ ባሻገር በተለያየ መልክና ቅርጽ ተዘጋጅቶ መቅረብ እንደሚችል ከማረጋገጣቸው ጎን ለጎን፤ በጤፍ የተዘጋጁት ምግቦች ያላቸው ጣዕም ከሃገሬው የምግብ ጣዕም ጋር የሚሄድ መሆኑን ተረዱ።

ሙከራው ተደርጎ አውንታዊ ውጤት መገኘቱን ተከትሎ ''ገበያውም ሆነ ተጠቃሚው ለጤፍ ያላቸውን አመለካከትና አቀባበልን ከተረዳሁ በኋላ የጤፍ ምርትን ወደ ፈረንሳይ ሃገር ለማስመጣት ወሰንኩ'' ትላለች ሩት።

ስለጤፍ ሲነሳ ቀድሞ ምንጩ ነው የሚታወሰው። ሩትም አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅትና ሙከራ ካደረገች በኋላ ጤፍን ወደማስመጣቱ ተሸጋገረች። ''ኢትዮጵያዊ እንደመሆኔ ጤፍ ከኢትዮጵያ ማስመጣት ብፈልግም በጣም ብዙ ውጣ ውረዶች ገጥመውኝ ነበር'' ትላለች።

በመቀጠልም ''የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላት የግብርና ሽግግር ኤጀንሲም ሄጄ ነበር። የዛሬ ሦስት ዓመት ጤፍ ከኢትዮጵያ ማስመጣት ይቻላል ተብሎ ወዲያውኑ ደግሞ ጤፍ ከሃገር እንዳይወጣ ተከለከለ'' ብላ ከዚያም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ጤፍ ወደ ፈረንሳይ ለመግባት ተገቢው ፈቃድ እንደሌለውም አጫውታናለች። ምክንያቱን ስታስረዳም የኢትዮጵያ ጤፍ ሙሉ በመሉ ተፈጥሮሯና ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን ማረጋገጫ ስለሌለው እንደሆነ ተናግራለች።

ይህ ማረጋገጫ የሚያስፈልገው ምርቱ ከተለያዩ ኬሚካሎች ንክኪ ነፃ መሆኑ በምርመራ ተረጋግጦ ለተጠቃሚው እንዲደርስ በፈረንሳይ የሚመለከተው ተቋም ፈቃድ አግኝቶ ወደሃገር ውስጥ እንዲገባ መፈቀድ ስላለበት ነው።

ተፈላጊውን ፈቃድ ለማግኘት መታለፍ ያለበት ሂደት ድግሞ ከ14 ሺህ ዬሮ በላይ ወጪን የሚፈልግ ጉዳይ ነው ብላለች ሩት። ይህም ደግሞ ለአንድ ኢትዮጵያዊ ጤፍ አምራች በጣም ከፍ ያለ ወጪ ነው።

ስለዚህም ይህ ሂደት ነው የኢትዮጵያን የጤፍ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ እንዳይቀርብ እንቅፋት የሆነባት። ''የጤፉ ምንጭ ከኢትዮጵያ ሆኖ ሌሎች ከእኛ በተሻለ እየሸጡ እንዲጠቀሙበት አድርጓል'' በማለት ትቆጣለች።

በዚህም ምክንያት ሥራዋን ከጀመረችና ደንበኞችን ካስለመደች በኋላ ምርቱን ማቅረብ ካልቻለች የንግድ ሥራዋን የሚያበላሽ ሆኖ ስለታያት ሌላ አማራጮችን መፈለግ ጀመረች። የጤፍ ምርትን ለማግኘትም ከኢትዮጵያ ውጪ ወደ ደቡብ አፍሪካና ወደ አውስትራሊያ ፊቷን ለማዞር ተገደደች።

Image copyright RUTH LISHANU
አጭር የምስል መግለጫ በጤፍ የተሠራ ብስኩትና ቸኮሌት

ከደቡብ አፍሪካ ያገኘችውን ጤፍ ወደ ፈረንሳይ ከማስመጣቷ በፊት ለመሞከር ወደዚያው ሄዳ ነበር። ጣዕሙም ከኢትዮጵያ ጤፍ ጋር ምንም ልዩነት እንደሌለው ተናግራለች።

ከዚህ በኋላ በምታስመጣው ጤፍ ፓንኬክ፣ ኬክ፣ ፓሰታ፣ ብስኩቶች እና ቸኮሌት የመሳሰሉት ምግቦች ይሠሩበታል። የጤፍ ይዘት ለጤና ተስማሚ ከመሆኑም ባሻገር የማያወፈር በመሆኑ ኬክም ሆነ ፓስታ ለመሥራት ተመራጭነት አለው። እነዚህንም ምርቶች 'አዲሲኒያ' በሚል ስያሜ ለገበያ አቅርባለች።

ሩት እንዳጫወተችን በፈረንሳይ ውስጥ ብዙ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ምግብ ቤቶች ቢኖሩም እሷ የምታስመጣውን ጤፍ አይጠቀሙም። ምክንያቱም ዋጋው ስለሚወደድ አብዛኛውን ጊዜ ከሩዝ የተሠራ እንጀራ መሸጥ እንደሚመርጡ ነግራናለች። ''ጤፍ ቢጠቀሙም እንኳን ከእስራኤል ወይም ከዮርዳኖስ ነው የሚያስመጡት።''

ከመጋዘን ሲወጣ 250 ግራም በ7 ዩሮ እንደሚሸጥ የነገረችን ሩት፤ ፈረንሳይ ሃገር ጤፍ በብዛት ስለማይገባ ዋጋው ውድ መሆኑንም አስረድታናለች። ገበያው እንደ አሜሪካና ጀርመን ሃገር አይደለም የምትለው ሩት፤ ዋጋው ከፍ እንዳለ ሊቆይ እንደሚችል ትላለች።

ሩት ይህንን ሥራ የጀመረችው የጤፍ ዱቄትን በማስመጣት ለመሸጥ ቢሆንም አሁን ግን ትኩረቷን ከጤፍ የተሠሩ ምርቶች ማቅረብ ላይ እያደረገች ነው።

በየስድስት ወሩ እስከ 300 ኪሎ ጤፍ ወደ ፈረንሳይ የምታስመጣው ሩት፤ የኢትዮጵያ ጤፍ ፈቃድ አግኝቶ ለገበያ ብታቀርብ ምርጫዋ እንደሆነ ተናገግራለች። ለጊዜው የምታቀርባቸውን ምርቶች ዓይነት የመጨመር ሃሳብ እንዳላትና ከፈረንሳይ በተጨማሪ ደግሞ ወደ ጣሊያን ሃገር የማከፋፈል ዕቅድ እንዳላት ነግራናለች።

አያቷ የጤፍ ነጋዴ እንደነበሩ የምታስታውሰው ሩት 'ለዚያ ሳይሆን አይቀርም ወደ ጤፍ ያዘነበልኩት' በማለት አጫውታናለች። በተጨማሪም አባቷ የነበራቸው የሆቴል ቤት ውስጥ ብዙ ጊዜዋን ታሳልፍ ስለነበር ለምግብ ዝግጅት ያላትን ፍቅር ሳያዳብርላት እንዳልቀረ ሩት ታስባለች።