የአይቤክስ እና ሮሃ ባንድ ጊታር አናጋሪ

ሠላም ስዩም Image copyright Selam

ሠላም ስዩም በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሙዚቃ ዕድገት ላይ የበኩሉን አስተዋፅኦ ያበረከተ እና አሁንም እያበረከተ ያለ የሙዚቃ ባለሙያ ነው።

ሠላም በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ስማቸው በጉልህ ሰፍሮ የሚታየው አይቤክስ እና ሮሃ ባንዶችን ከማቋቋሙም በላይ ጊታሩን ይዞ ከጥላሁን ገሠሠ፣ ከአለማየሁ እሸቴ፣ ከማህሙድ አህመድ እንዲሁም ከሂሩት በቀለ ጋር ተጫውቷል።

ከእነዚህ ቀደምት ድምፃዊያን በተጨማሪ ከአስቴር አወቀ እና ነዋይ ደበበ እንዲሁም የዘመናዊ ሙዚቃ ፈርጥ ተብሎ ከሚታወቀው ከቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ጋርም መጫወት ችሏል።

የሠላም የሙዚቃ አጨዋወት ስልት እጅግ የተለየና ለስላሳ እንዲሁም ረቂቅ የሙዚቃ ስልቶች እንደሚንፀባረቁበት ይነገራል። የቢቢ ኪንግና ሳንታና ሙዚቃዎችን የሚያደምጡ ሰዎች የሠላምን ሙዚቃ ለመረዳት አያዳግታቸውም። እነሱን እየሰማ እንዳደገም ይናገራል።

የሠላምን ሙዚቃ በደንብ ለማጣጣም፤ ለቀድሞው ጓደኛው ተክሌ ተስፋዝጊ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ የሰራቸውን 'ከምድላዬ'፣ 'ፍቅረይ ተለመኒ' እንዲሁም 'ንንገሮም ንስድራና' የተሰኙ የትግርኛ ሙዚቃዎችን መስማት በቂ ነው። እነዚህ የሠላም መሪ ጊታር ተጫወችነት ጎልቶ የወጣባቸው ሥራዎች ናቸው።

ሠላም በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች የተዘዋወረ ሲሆን ከተለያዩ ባለሙያዎች ጋር ዓለም አቀፍ ሙዚቃዎችን ሰርቷል። አሁን ላይ ከሚሰራቸው ሙዚቃዎች ባለፈ አባቱን የሚዘክርበት ፕሮጀክት ላይ አትኩሮ ይገኛል።

የአባ ተፅዕኖ

የሠላም አባት ስዩም ወደልማርያም አይነ-ስውር ነበሩ። ቢሆንም አስደናቂ የሆነ ሕይወት ከመምራት ወደኋላ አላሉም። በዚህ የሕይወት ጉዟቸው ደግሞ ባለቤታቸውና ቀኝ እጃቸው የነበሩት የወ/ሮ ፅርሃ ነማርያም ህድሩ አስተዋፅኦ ጉልህ ነበር። አቶ ስዩም በኢትዮጵያ እና ኤርትራ የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት በማቋቋምና በመምራት ይታወቃሉ።

Image copyright Selam

1950ዎቹ ላይ አንድ ቀን አቶ ስዩም ወደ ንጉሡ ጠጋ ብለው ለዓይነ ስውራን የሚሆን ትምህርት ቤት ሊያቋቁሙ እንዳሰቡ አጫወቷቸው። ንጉሡም "እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ ይሁን" አሉ። ከዚያም በአውሮፓውያኑ 1952 የዓይነ ስውራን ተማሪ ቤት ተቋቋመ።

አዲስ አበባ ለሚገኘው መካነ ኢየሱስ እና ለአስመራው ወንጌላዊት ቤተ-ክርስትያን መመስረት ያደረጉት አስተዋፅኦም ፍፁም አይዘነጋም።

አቶ ስዩም ድንቅ የሙዚቃ ችሎታ የነበራቸው ሙዚቀኛም ነበሩ። ቢሆንም ዓለማዊ ሙዚቃ ለመጫወት ብዙም ፈቃደኛ አልነበሩም። ሠላምም ከዚህ ተፅዕኖ ባይወጣም እያደገ ሲመጣ ወደ ዓለማዊው ሙዚቃ መሳብ ጀመረ።

ከልጅነት እስከ እውቀት

ከስድስት የቤተሰቡ ልጆች አራተኛው የሆነው ሠላም የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈው ካዛንቺስ ነበር። በልጅነት ሕይወቱ ኃይለማርያም የተባለ ዓይነ ስውር ጓደኛውና ዳንኤል የተባለ አሜሪካዊ ወዳጁ ትልቅ ድርሻ ነበራቸው።

"ስለ ልጅነቴ ሳስብ ሁሌም የማይዘነጋኝ የካዛንቺስ ሕይወቴና ከዚያም የአስመራ ቆይታዬ ነው" ይላል ሠላም። አስመራም አዲስ አበባም በሚገኙት የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤቶች ተምሯል፤ ከቤተ-ክርስትያን ደጃፍም አይጠፋም ነበር።

ከአዲስ ወደ አስመራ

በአውሮፓውያኑ 1965 ወደ አስመራ ያቀናው ሠላም "ብዙ ነገሮች አዲስ ሆኑብኝ" ሲል የነበረውን ያስታውሳል። የዛኔዋ አስመራ እጀግ ዘመናዊ ነበረች። ቃኘው የተመደቡ አሜሪካውያን እንዲሁም ጣልያኖች ከተማዋን አውሮፓ አስመስለዋት ነበር ይላል ሠላም። "ይህም ሙዚቃን ከዚህም ከዚያም እንድሰማ ምክንያት ሆነኝ።"

ሠላም አስመራ እያለ አምስት አባላት ያሉት የሙዚቃ ቡድን አቋቋመ። ቡድኑ በዋናነት የቤተ-ክርስቲያን ዝማሬዎችን የሚጫወት ነበር። በተለይ በወንጌላዊት ቤተ-ክርስቲያን አማኞች ዘንድ እውቅናን አተረፈ። በርካታ ወጣት ተከታዮችንም ማፍራት ቻለ።

ምንም እንኳ ወጣት አማኞች የእነሠላምን ቡድን ሙዚቃ ቢወዱትም በዕድሜ ገፋ ያሉ የቤተ-ክርስቲያኗ ተከታዮች ቡድኑ እንዲዘጋ ጠየቁ። ይህም የቡድኑን መጨረሻ አፋጠነው። "እንደዛ ከፍቶኝ አያውቅም" በማለት ሠላም ሁኔታውን ያስታውሳል።

በዚያን ወቅት የልጅነት ጓደኛው ኃይለማርያም፤ ሳባ የተሰኘ ባንድ አቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ ነበር። ሠላምም ወደ ልጅነት ጓደኛው ተመለሰ።

በአውሮፓውያኑ 1973 ሳባ ባንድ ወደ ብላክ ሶል ባንድ ስሙን በመቀየር አዲስ አበባ ላይ በመዘዋወር የሙዚቃ ዝግጅቶችን ማቅረብ ጀመረ። ሠላምም ቡድኑን ተቀላቀለ። በዚያ ወቅት ቡድኑ በአዲስ አበባ ዝናው የናኘበት ወቅት ነበር። በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ሥራዎቻቸው ቀርበዋል።

ታድያ አንድ ቀን ሠላም አባል የሆነበት ባንድ ሥራዎች በቴሌቪዥን በሚቀርቡበት ወቅት፤ አባቱን ጨምሮ የቤተሰቡ አባላት ሰብሰብ ብለው እየተከታተሉ ነበር። የሠላም አባት ልጃቸው ጊታሩን ይዞ በቴሌቪዥን መታየቱን ሲገነዘቡ ብስጭታቸውንም መደበቅ አልቻሉም። ይህን የተረዳው ሠላም በሙዚቃው በመግፋት ቤተሰቦቹን ለማሳመን ጉዞውን ያዘ።

Image copyright Selam

አይቤክስ እና ሮሃ...

ሠላምን የሚያውቁት ሁሉ እሱን ከአይቤክስ ባንድ ጋር ማያያዛቸው የማይቀር ነው። አይቤክስ ባንድ በዚያን ጊዜ ይሰራ የነበረው አዲስ አበባ ውስጥ አሉ በተባሉት እንደ ራስ ያሉ ሆቴሎች ውስጥ ነበር። ያን ጊዜም መላ መላ የተሰኘው የማህሙድ አህመድ ሥራ የተለቀቀበት ጊዜም ነበር።

ቢሆንም አይቤክስ ባንድ ብዙም አልቆየም። ከጥቂት ዓመታት በኋላ የባንዱ አባላት ሃገር ጥለው በመሄዳቸው ምክንያት ለመፍረስ በቃ። ይህን ጊዜ ሠላም ሌላ ባንድ መቋቋም እንዳለበት ራሱን አሳምኖ መንቀሳቀስ ጀመረ። ከዚያም ሮሃ ባንድ ተመሰረተ። ሠላም በሮሃ ባንድ ውስጥ ሙዚቃ ከመጫወት ባለፈ የማስተዳደር ሥራም ይሰራ ነበር።

በ60ዎቹ እና 70ዎቹ ውስጥ በነበሩት ጊዜያት ብቻ አይቤክስ እና ሮሃ ባንዶች በሺዎች የሚቆጠሩ ሙዚቃዎችን አቀናብረዋል፤ አሳትመዋል። በእነዚህ ሁሉ ሂደቶች ታዲያ ሠላም ትልቅ ሚና መጫወቱ አልቀረም።

አዲስ አበባ ውስጥ አምስት ኪሎ አካባቢ ተወልዶ ያደገው ሠላም፤ ለሙዚቃ ያለውን ፍቅር በብዙ መልኩ ገለፀ ሙዚቃም ውለታውን አልነፈገችውም። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ክፍል ውስጥ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ ትኩረት በማድረግ አጥንቷል። ቁጥራቸው ከበዛ የሙዚቃ ባለሙያዎች ጋርም ሠርቷል።

በስተመጨረሻም ሠላም ወደ አሜሪካ በማቅናት ከበርካታ የሙዚቃ ሰዎች ጋር በመተባበር ሌሎች ተጨማሪ ሥራዎችን ለሙዚቃ አፍቃሪው ማበርከት ችሏል።

ሠላም ጥንካሬ አሁንም አልተለየውም። ልክ እንደሙዚቃ እሱም የሚያረጅ አይመስልም። ሠላምን ያገኘነው በካሊፎርንያ ክፍለ ግዛት ውስጥ ከኤፍሬም ታምሩ ጋር የሙዚቃ ድግስ በሚያዘጋጅበት ወቅት ነበር።

ተያያዥ ርዕሶች