"የእንግሊዙ ተቋም በኬንያ ዳግመ ምርጫ ጣልቃ ገብቷል"

"የኬንያ ዳግመ-ምርጫ ተጭበርብሯል" Image copyright AFP

ኡሁሩ ክንያታ የኬንያ ዳግማዊ ምርጫ እንዲያሸንፉ ረድቷል የተባለው የእንግሊዙ 'ካምብሪጅ አናሊቲካ' አማካሪ ተቋም ላይ ሙሉ ምርመራ ሊካሄድ ይገባል ሲሉ የሃገሪቱ ተቃወዋሚዎች እየከሰሱ ነው።

ናሽናል ሱፐር አላያንስ (ናሳ) የተሰኘው የኬንያ ዋነኛ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ባለሥልጣን የሆኑት ኖርማን ማጋያ የተሰኙ ግለሰብ ለቢቢሲ አንደተናገሩት ገዢው ፓርቲና አማካሪው ተቋም የህዝብን ድምፅ በመስረቅ ወንጀል ሊከሰሱ ይገባል።

የአማካሪ ተቋሙ ኃላፊዎች በኬንያ ምርጫ የነበራቸውን ሚና በኩራት ሲያወሩ ሳያስቡት በካሜራ እይታ ወስጥ ከገቡ በኋላ ነው ሁኔታው ቀልብ መግዛት የጀመረው።

ተቋሙ በሂደቱ ውስት እጄ የለበትም ሲል ማስተባበሉ አልቀረም።

ገዢው ጁቢሊ ፓርቲ ሁኔታውን ያጣጣለው ሲሆን አማካሪ ድርጅቱ ለማስታወቂያ ሥራ የተቀጠረ እንጂ ለሌላ ጉዳይ የመጣ አይደለም ብሏል።

የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ዳቪድ ሙራቴ ለሮይተርስ ዜና ወኪል ሲናገሩ "ድርጅቱ የፓርቲያችንን አርማ ማስታወቂያ ለመስራት የመጣ እንጂ ህግ ወጥ ተግባር ሊፈፅም የተቀጠረ አይደለም" ብለዋል።

ተቋሙ በመገናኛ ብዙሃን ዓይን ውስጥ መግባት የጀመረው የአሜሪካው ፕሬዙደንት ዶናልድ ትራምፕ ወደስልጣን እንዲመጡ አግዟል የሚል ወሬ መስፋፋት ከጀመረ ወዲህ ነበር። ከፌስቡክ ላይ የሰዎችን ግላዊ መረጃ ያለፈቃዳቸው ወስዷል በሚልም እየተከሰሰ ይገኛል።

አከራካሪ ጉዳዮች ያልተለዩት የኬንያ ምርጫ በወርሃ ሰኔ ከተካሄድ በኋላ ኡሁሩ ማሸነፋቸው ተነግሮ ነበር። ነገር ግን ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት የወሰዱት ተቃዋሚው ኦዲንጋ ተሳክቶላቸው ምርጫው በፍርድ ቤት ውድቅ ሆኖ ድጋሚ እንዲካሄድ ተወሰነ።

በዳግመ-ምርጫው ወቅት ሁኔታዎች አሁንም ፍትሃዊ አይደሉም ያሉት ኦዲንጋ ምርጫውን አቋርጠው ወጡ፤ ኡሁሩም ድጋሚ አሸነፉ።

በቅርቡ ግን የማይታሰብ የሚመስለው ሆነ። ኦዲንጋ እና መሪው ኡሁሩ ተቃቅፈው ታዩ። ልዩነቶቻችንን ለመፍታት ጠንክረን እነሠራለን ሲሉም ተደመጡ።

ምንም እንኳ አሁን ላይ በሁለቱ ግለሰቦች መካከል ያለው ግንኙነት መልካም ቢመስልም የናሳው ማጋያ መሰል ማጭበርበሮች ለኬንያ ዴሞክራሲ ዕድገት ፀር ናቸው በማለት ነው እየከሰሱ ያሉት።