እስር በአዲስ አበባ እና በባህር ዳር

እስክነድር ነጋ

የፎቶው ባለመብት, facebook

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ በቅርቡ ከእስር የተፈቱ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያንና ፖለቲከኞች አዲስ አበባ ውስጥ በፖሊስ ትናንት መያዛቸው ተዘገበ።

በተመሳሳይም በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህር ዳር ውስጥ በርካታ ምሁራንና ፖለቲከኞች ቅዳሜ ዕለት በፖሊስ እንደተያዙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ቤት በተዘጋጀ ማህበራዊ ሥነ-ሥርዓት ላይ ታዳሚ ከነበሩትና በፖሊስ ከተያዙት መካከል ከሳምንታት በፊት ከረዥም እስር በኋላ የተፈቱት ተመስገን ደሳለኝን ጨምሮ እስክንደር ነጋ፣ አንዷለም አረጌ እና ዘላላም ወርቃገኘሁ የሚገኙበት ሲሆን፤ ማህሌት ፋንታሁ፣ በፍቃዱ ኃይሉ፣ ወይንሸት ሞላ፣ አዲሱ ጌትነት፣ ይድነቃቸው አዲስ፣ ስንታየሁ ቸኮል እና ተፈራ ተስፋዬ የተባሉ ግለሰቦች ትናንት ምሽት ተይዘዋል።

ፖሊስ የያዛቸውን ሰዎች በአቅራቢያው ወደሚገኝ ጣቢያ ወስዶ ምርመራ ያደረገላቸው ሲሆን፤ መሰብሰብ እንደማይቻልና ማስፈቀድ እንደነበረባቸው ለታሳሪዎቹ እንደተነገራቸው ከታሳሪዎቹ ቤተሰብ አንዱ ተናግሯል።

በዝግጅቱ ስፍራ ተሰቅሎ ነበር የተባለው የኮከብ ምልክት የሌለው ባንዲራ ፖሊሶች በስፍራው እንደደረሱ ያለመግባባቱ መነሻ የነበረ ሲሆን በፖሊስ ጣቢያ ውስጥም እንደመጀመሪያ ክስ ቀርቧል።

የተያዙት ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያንና ፖለቲከኞች ቀድሞ በተወሰዱበት ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ቃላቸውን ከሰጡ በኋላ ወደሌላ ፖሊስ ጣቢያ ከመሸ በኋላ መዘዋወራቸውን የተመስገን ደሳለኝ ወንድም ገልጿል።

ታሳሪዎቹ ሳይፈቱ በፖሊስ ጣቢያ ሌሊቱን እንዳሳለፉ ቤተሰቦቻቸውና ጓደኞቻቸው ገልፀዋል።

በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት መጠናቀቂያ በባህር ዳር ከተማ የታሰሩት ከአስራ አምስት በላይ ግለሰቦች ህጋዊ ፓርቲ የማቋቋም ሒደት ላይ እንደነበሩ ተነግሯል።

የፓርቲው መስራች ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ክርስትያን ታደለ ለቢቢሲ እንደገለፁት ኮሚቴው የምርጫ ቦርድ ይሁንታ አግኝቶ እንቅስቃሴ ከጀመረ ከአራት ወራት በላይ ተቆጥረዋል።

ያለፉትን ጥቂት ወራት የፓርቲውን መርኃ ግብር እና መተዳደሪያ ደንብ ረቂቆች ሲያሰናዱ እንዲሁም የቅድመ-መስረታ ጉባዔ እንቅስቃሴዎችን ሲያከናውኑ እንደቆዩ የሚናገሩት አቶ ክርስትያን፤ መስራች ጉባዔውን መቼ እና የት እናከናውን በሚለው ጉዳይ ላይ ለመምከር ነበር በባህር ዳር ከተማ የተሰበሰቡት።

በተያያዘም ሥራ ላይ ያለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሚያስፈፅመው ግብረ ኃይል ጥያቄ የማቅረብ ዕቅድ እንደነበራቸውም ይገልፃሉ።

ከፓርቲው መሥራቾች በተጨማሪ በስፍራው የነበረ የክልሉ ጋዜጠኛ መታሰሩን የሚገልፁት አቶ ክርስትያን፤ እርሳቸው ለሥራ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚገኙ በመሆኑ በቦታው እንዳልተገኙ ሆኖም ከባልደረቦቻቸው ባገኙት መረጃ መሰረት ታሳሪዎቹ በሚያዙበት ወቅት ድብደባ እንደነበረ መረዳታቸውን ለቢቢሲ ጨምረው ተናግረዋል።