ፌስቡክ ከባድ ቅጣት ሊያስከትል የሚችል ምርመራ ሊደረግበት ነው

ፌስቡክ Image copyright Reuters

ፌስቡክ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የተጠቃሚዎቹን ግላዊ መረጃ ኬምብሪጅ አናሊቲካ ለተባለው ተቋም እንዴት አሳልፎ እንደሰጠ በአሜሪካ ፌደራል የንግድ ኮሚሽን አማካይነት ምርመራ ሊደረግበት ነው።

የማህበራዊ ትስስር መድረክ የሆነው ፌስቡክ 50 ሚሊዮን የሚሆኑ ተጠቃሚዎችን መረጃን ለትንተና ተቋም አሳልፎ በመስጠቱ ለወቀሳ ተዳርጓል።

ተላልፎ የተሰጠው መረጃ ዶናልድ ትራምፕ ለፕሬዝዳንትነት ላካሄዱት የምረጡኝ ዘመቻ ጥቅም ላይ ውሏል ተብሎ ይታመናል።

ምርመራውን የሚያካሂደው መንግሥታዊ ተቋም ፌስቡክ የተጠቃሚዎቹን መረጃ ለምን መጠበቅ ሳይችል እንደቀረ ማጣራት ያደርጋል።

በምርመራው ፌስቡክ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ በትሪሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ቅጣትን ሊያስከትልበት እንደሚችል አንድ የምርመራ አድራጊው ተቋም የቀድሞ ባለስልጣን ተናግረዋል።

ፌስቡክ የተጠቃሚዎቹን መረጃ በሌሎች ከመወሰዱ በፊት ማሳወቅና የተጠቃሚዎቹን ፈቃድ መግኘት እንደሚገባው በህግ ይገደዳል።

በንግድ ኮሚሽኑ ውስጥ የተጠቃሚዎች ጥበቃ ቢሮ የቀድሞ ዳይሬክተር የሆኑት ዴቪድ ቭላዴክ እንደሚሉት በእያንዳንዱ ተጠቃሚ ላይ ለተፈፀመው የመብት ጥሰት 40 ሺህ ዶላር ቅጣት ፌስቡክን ሊጠብቀው ይችላል።

በእርግጥም እንደተባለው የ50 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ግላዊ መረጃ ተላልፎ የተሰጠ ከሆነ ፌስቡክ በትሪሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ቅጣት ይጠብቀዋል ሲሉ ቭላዴክ ለዋሽንግተን ፖስት ተናግረዋል።

የፌስቡክ ባለቤት ማርክ ዙከርበርግ በተከሰተው ችግር ዙሪያ ቀርቦ እንደተናገረው "ይህ እምነትን የማጉደል ነው፤ በዚህም አዝናለሁ" ብሏል።

በተጨማሪም ድርጅቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች ግላዊ መረጃ ወደ ሌሎች እንዳይተላለፉ ለማድረግ የበለጠ ማድረግ ይችል እንደነበር አምኗል።

ይህንን ተከትሎም ፌስቡክ ተመሳሳይ የመረጃ መሹለክ በድጋሚ እንዳይከሰት አስፈላጊ የተባሉ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን አሳውቋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ