ችላ የተባሉትን ለመርዳት የሚጥረው ወጣት

የሰፈሩ ሰዎች አስምሮም እያሉ ይጠሩታል። ሙሉ የመዝገብ ስሙ አስመረ ተፈራ ነው። ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ በርበሬ ተራ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ነው።

በልጅነት እድሜው ወላጆቹ ስለተለያዩ በጎዳና ላይ ነበር ያደገው። በጨቅላ እድሜው ያሳለፈው የጎዳና ህይወት በብዙ ውጣ ውረዶች የተሞላ እንደነበረ አስመሮም ያስታውሳል። ጎዳና ላይ ይኖር በነበረበት ወቅት ከቦታ ቦታ እየተንከራተቱ ትኩረት የተነፈጋቸውን የአእምሮ ህሙማንን የመርዳት ፍላጎት እንዳደረበት ይናገራል።

በአሁኑ ወቅት አስመሮም መርካቶ ሲኒማ ራስ አካባቢ ባለው ከቆርቆሮ ከተሰራ አነስተኛ እና አጭር ቤት ውስጥ ከመንገድ ዳር ይኖራል። ''ከልጅነቴ ጀምሮ በጎዳና ላይ የሚኖሩ የአእምሮ ህሙማንን የመርዳት ፈላጎት ነበረኝ። ይህንም ማድረግ የጀመርኩት ገላቸውን በማጠብ ነው'' ሲል ይናገራል።

እንደ እሱ እምነት ከሆነ ሰውን ለመርዳት እውነተኛ ፈላጎት ብቻ በቂ ነው። ''በገንዘብ ወይም በእውቀቴ መረዳት አልቻልኩም። የነበረኝ ጉልበት ብቻ ነው። ስለዚህ ገላቸውን በማጠብ ጀመርኩ'' ሲል የበጎ ሥራውን አጀማመር ያስታውሳል።

አስመሮም ከዓመታት በፊት አንድ የአእምሮ ህመምተኛን ገላ ካጠበ በኋላ፤ በዚህ ተግባሩ በመቀጠል በሳምንት ከሰማኒያ በላይ የሚሆኑ ህሙማንን ለመንከባከብ እሏል። ይህን ብቻውን መድረግ እንደማይችል ሲረዳ ''ብዛታቸው 85 ሲደርስ በጣም ከበደኝ ስለዚህ ሊረዱኝ ፈቃደኛ የሆኑ ወጣቶችን ማሰባሰብ ጀምርኩ'' ይላል።

የአስመሮምን ጥሪ በመቀበል የተለያዩ ሥራዎችን በመስራት ከሚግዙት መካከል አንዱ ያሬድ ፋንታሁን ነው። የያሬድ ሃላፊነት ጎዳና ላይ የሚገኙ ተማሪዎችን ከመደበኛ ትምህርት መልስ ማስጠናት ነው። ያሬድ ይህን ሲሳራ ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ወደ አስራ ሁለት የሚጠጉ ጎዳና ላይ የሚኖሩ ህጻናትን ያስጠናል።

በአሁኑ ወቅት አስመሮምና ጓደኞቹ ከሚኖሩበት አካባቢ አቅራቢያ በሚገኝ ሜዳ ላይ በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ ወደ 300 የሚጠጉ ህሙማንን ገላቸውን በማጠብ፣ ፀጉራቸውን በማስተካከል እና የገዙትንና ከተለያዩ ለጋሾች የሰበሰቧቸውን አልባሳት በማልበስ ይሸኟቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ዘውትር ምሳ ሰዓት ላይ ደጋፊ የሌላቸውን ህጻናት እና አዛውንቶችን ይመግባል። ''በየቀኑ ለምሳ 60 እንጀራ እገዛለሁ። የተራቡ ህጻናት እና ሰርተው መብላት የማይችሉ አዛውንቶችን በተቻለ እንዳይራቡ ለማድረግ እሞክራለሁ'' ሲል ይናገራል።

ይህን በጎ ተግባሩን ላለፉት ስምንት ዓመታት ሲያከናውን የቆየው አስመሮም፤ በቋሚነት መኪኖችን የመጠበቅ ሥራ ነው ያለው።

ለሚያከናውናቸው በጎ ተግባራት ወጪውን እንዴት እንደሚሸፍን ሲያስረዳ ''በአካባቢዬ ከሚገኝ ምንጭ ውሃ እያወጣሁ እሸጣለሁ፣ ከዚህ በላይ ግን በገንዘብ እና በሞራል ከፍተኛ ድጋፍ የሚያደርጉልኝ ሥራዬን የሚያውቁ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ በአካባቢዬ የሚገኙ ነጋዴዎች እና ሥራችንን የሚመለከቱ አላፊ አግዳሚ መንገደኞች ጭምር ድጋፍ ያደርጉልናል'' ይላል።

ምንም እንኳ ይህ የአስመሮም እና ጓደኞቹ ተግባር ለአእምሮ ህሙማኑ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ባይሰጥም ''ቢያንስ ተባይ እንዳይበላቸው ገላቸውን አጥበን ንጹህ ልብስ አልብሰን እና መግበናቸው እንለቃቸዋለን'' ይላል።

አስመሮም የአእምሮ ህሙማኑን ገላቸውን አጥቦ አዲስ ልብስ ካለበሰ በኋላ ፎቶ የማንሳት ልምድ አለው። ''ይህን የማደርገውም በርካታ ህሙማን ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው አንዳንዶቹም ጠፍተው ነው ጎዳና ላይ የሚንከራተቱት፤ ስለዚህ ቤተሰቦች የጠፉባቸውን ሰዎች ለመፈለግ እኔ ጋር ሲመጡ ፎቶግራፎቹን ይመለከታሉ።''

በዚህም የጠፉባቸውን የቤተሰብ አባላቸውን ማግኘት የቻሉ ሰዎችም እንዳሉ አስመሮም በማለት ይናገራል።