ዶ/ር አብይ አህመድ የኢህአዴግ ሊቀ-መንበር ሆነው ተመረጡ

Image copyright OPDO Official
አጭር የምስል መግለጫ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ዶ/ር አብይ አህመድ

ዶ/ር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀ-መንበር ሆነው ተመረጡ።

የኦህዴድ ሊቀ-መንበር ሆነው በቅርቡ የተመረጡት ዶ/ር አብይ የኢህአዴግ ሊቀ-መንበር ሆነው በመመረጣቸው ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው የመሰየም እድላቸው የሰፋ እንደሆነ ተነግሯል።

በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት መሰረት ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መካከል የሚመረጥ ይሆናል። ከዚህ ቀደም በነበረው ልምድ መሰረት የፓርቲው ሊቀ-መንበር የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ሆኖ ሲሾም ቆይቷል።

ከመጋቢት 11 ቀን 2010 ዓም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ፤ ዛሬ የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ከሊቀመንበርነት ልልቀቅ ጥያቄ በሙሉ ድምፅ ተቀብሎ ዶ/ር አብይ አህመድን አዲሱ የኢህአዴግ ሊቀ-መንበር አድረጎ ሾሟል።

የኢህአዴግ ምክር ቤት የብአዴን ሊቀ-መንበር የሆኑትን አቶ ደመቀ መኮንን የድርጅቱ ምክትል ሊቀ-መንበር ሆነው ባሉበት እንዲቀጥሉ ወስኗል።

ዶ/ር አብይ አህመድ ማናቸው?

ዶክተር አብይ አህመድ በአጋሮ ከተማ የተወለዱ ሲሆን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ አግኝተዋል።

ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ሰርተዋል።

በግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ እና በሊደርሺፕ ተቋም ደግሞ የሥራ አመራር ሳይንስ አጥንተዋል። እንዲሁም አሽላንድ ዩኒቨርሲቲ በንግድ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪ ያገኙ ሲሆን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰላም እና ደህንነት ጥናት ፒኤችዲ አላቸው።

በመጀመሪያ 40ዎቹ የሚገኙት ዶክተር አብይ ኦህዴድን የተቀላቀሉት በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው። ከፖለቲካ ተሳትፏቸው በተጨማሪ በወታደራዊ ጉዳዮች ሰፊ ተሳትፎ የነበራቸው ሲሆን የሌተናል ኮሎኔል ማዕረግ አላቸው።

በተባበሩት መንግሥታት የስላም ማስከበር ተልዕኮን ለማስፈጸም ሩዋንዳ ዘምተዋል።

ከ2000 እሰከ 2003 የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ መስራች እና ዳይሬክተር በመሆነ አገልግለዋል። ከዚያም የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚንስትር በመሆን ሰርተዋል።