ቻይናና ሰሜን ኮሪያ ኪም ጆንግ ኡን ግብኝት ማድረጋቸውን አረጋገጡ

ኪም ጆንግ ኡን በቻይና Image copyright CCTV

ማንተቱ ያለተገለፀ የሰሜን ኮሪያ ከፍተኛ ባለስልጣን ቻይናን መጎብኘቱ ከተገለፀ ከቀናት በኋላ የሃገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን መሆናቸው ተረጋገጠ።

ኪም ጆንግ ኡን ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የታወቀ የውጪ ሃገር ጉብኝታቸው እንደሆነ የተነገረውን ይህን ጉብኝት መደረጉን የቻይናና የሰሜን ኮሪያ ባለስልጣናት አረጋግጠዋል።

የቻይናው ዜና ወኪል ዢንዋ እንደዘገበው ኪም ከቻይናው አቻቸው ዢ ጂንፒነግ ጋር ቤይጂንግ ውስጥ "ስኬታማ ውይይት" እድርገዋል።

ቻይና የሰሜን ኮሪያ ዋነኛ የኢኮኖሚ አጋር ስትሆን፤ የጉብኘኝቱ አላማም ሰሜን ኮሪያ ከደቡብ ኮሪያና ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ለማድረግ ስላቀደችው ንግግር ከቤይጅንግ ጋር ለመመካከር ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።

ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡን በመጪው ሚያዚያ ከደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ሙን ጃኢ-ኢን ጋር እንዲሁም በግንቦት ወር ደግሞ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራመፕ ጋር ይገናኛሉ ተብሏል።

ኪም ጆንግ ኡን በቻይና ያደረጉት ጉብኝት ለታቀዱት ውይይቶች ከሰሜን ኮሪያ በኩል እየተደረገ ያለ ወሳኝ ዝግጅት እንደሆነ ተገምቷል።

በጉብኝቱ ወቅት ኪም ጆንግ ኡን ለቻይናው አቻቸው የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ግንባታ እቅዳቸውን እንደሚያቆሙ ማረጋገጫ እንደሰጡ፤ ነገር ግን መሟላት ያሉባቸውን ነገሮችንም እንዳስቀመጡ የቻይናው ዜና ወኪል ዘግቧል።

"የኮሪያ ልሳነ ምድርን ከኒውክሌር ነፃ ለመድረግ ደቡብ ኮሪያና ዩናይትድ ስቴትስ ከቀናነት በመነጨ ሁኔታ ለምናደርገው ጥረት ምላሽ መስጠት ይኖርባቸዋል። ሰላምን በአካባቢው እውን ለማድረግም የተቀናጁ ተከታታይ እርምጃዎችን በመውሰድ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን ይቻላል" ሲሉ ኪም ጆንግ ኡን መናገራቸው ተዘግቧል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ