ፈረንሳይ ህፃናት በሦስት ዓመታቸው ትምህርት እንዲጀምሩ ወሰነች

ተማሪዎች Image copyright Getty Images

ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮ ባስተዋወቁት አዲስ ለውጥ መሰረት በፈረንሳይ ውስጥ የሚገኙ ህፃናት ትምህርት መጀመር የሚገባቸው ስደስት ዓመት መሆኑ ቀርቶ በሦስት ዓመታቸው እንዲሆን ተደረገ።

ይህ ለውጥ በአውሮፓ ውስጥ በዝቅተኛ እድሜ ትምህርት በማስጀመር ፈረንሳይን ቀዳሚ ሀገር ያደርጋታል።

ነገር ግን አብዛኞቹ ፈረንሳያዊያን ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት የሚያስገቡት በሦስት ዓመታቸው ስለሆነ ይህ ውሳኔ ውስን ቁጥር ያለቸውን ወላጆች ብቻ ነው የሚመለከተው።

የፈረንሳይ መንግሥት መረጃ እንደሚያመለክተው 2.4 በመቶ የሚሆኑ ልጆች ብቻ ናቸው ከሦስት ዓመታቸው በኋላ ወደ ትምህት ቤት የሚገቡት።

ፕሬዝዳንት ማክሮ እንዳሉት ለውጡ ያስፈለገው በፈረንሳይ ውስጥና ፈረንሳይ በሌሎች አካባቢዎች ባሏት ግዛቶች ውስጥ ያሉ ድሃ ዜጎች ልጆቻቸውን በለጋ ዕድሜያቸው ወደ ትምህርት ቤት የሚያስገቡበት ዕድል ዝቅተኛ ስለሆነ፤ በሃገሪቱ ውስጥ ያለውን የትምህርት ዘርፍ ልዩነት ለማጥበብ ነው።

በአውሮፓ ሃገራት ህፃናት ትምህርት የሚጀምሩበት ዕድሜ

አራት ዓመት፡ ሰሜን አየርላንድ

አምስት ዓመት፡ እንግሊዝ ፣ ስኮትላንድ፣ ዊልስ፣ ቆጵሮስ፣ ማልታ

ስድስት ዓመት፡ ኦስትሪያ፣ ቤልጂየም፣ ክሮሺያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ዴንማርክ፣ ጀርመን፣ ግሪክ፣ ሃንጋሪ፣ አይስላንድ፣ የአየርላንድ ሪፐብሊክ፣ ጣሊያን፣ ሌሽቴንስታይን፣ ሉክሰምበርግ፣ ኔዘርላንድስ፣ ኖርዌይ፣ ፖርቱጋል፣ ሮማኒያ፣ ስሎቫኪያ፣ ስፔን፣ ስዊትዘርላንድ፣ ቱርክ

ሰባት ዓመት፡ ቡልጋሪያ፣ ኢስቶኒያ፣ ፊንላንድ፣ ላቲቪያ፣ ሉቱዋንያ፣ ፖላንድ፣ ስርቢያ፣ ስዊዲን