ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰዎች ምን ይጠብቃሉ?

አቶ የሽዋስ አሰፋ፡ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበር እና አቶ በቀለ ገርባ፡ የኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ-መንበር Image copyright FACEBOOK/BLUE PARTY & getty images

የኢህአዴግ ምክር ቤት ለሳምንት ካደረገው ስብሰባ በኋላ ዶ/ር አቢይ አህመድን የድርጅቱ ሊቀ-መንበር አድርጎ መምረጡን ይፋ አድርጓል። በዚህም ዶ/ር አቢይ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ከስልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ ካቀረቡበት ዕለት አንስቶ ማን ሊተካ ይችላል የሚለው ጥያቄ በሃገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ላይ ዋነኛ ጉዳይ ሆኖ ከአንድ ወር በላይ ቆይቷል።

ዶ/ር አብይ አህመድ የገዢው ፓርቲ ሊቀ-መንበር ሆነው በመመረጣቸው የተለያዩ ሰዎችን አስተያየትና ምን እንደሚጠብቁ ጠይቀናል።

አቶ የሽዋስ አሰፋ፡ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበር

የሚመረጠው ጠቅላይ ሚኒስትር ማንም ይሁን ማን መሆን ያለበት የህዝቡን ጥያቄ የተረዳና አስፈላጊውን ለውጥ ሊያግዝ የሚችል መሆን አለበት።

ዶ/ር አብይ አህመድም በሃገሪቱ ውስጥ ያለውን የለውጥ ፍላጎትና እንቅስቃሴ በደንብ ይረዱታል።

መጀመሪያ የቀሩተን የፖለቲከኞችና የህሊና እስረኞችን ሙሉ በሙሉ መፍታት፤ ሁለተኛው ደግሞ እነርሱን ጨምሮ ሁሉን አቀፍ ውይይት ማድረግ ከዚያም መስተካከል ያለባቸውን ተቋማት አስተካክሎ ህዝቡ በመረጠው እንዲተዳደር ማድረግ ናቸው።

በኦህዴድ አካባቢ ለህዝቡ ጥያቄ የተሻለ ግንዛቤ ነበር። ዶ/ር አቢይም ከዚህ በፊት ባደረጉት ንግግር ለህዝቡ ጥያቄ ቀና ምላሽ እንዳላቸው ገልጠዋል። እንግዲህ አሁን ይህንን ጥያቄ የሚመልሱበት ታሪካዊ አጋጣሚ ላይ ይገኛሉ ሲሉ መልካም እኞታቸውን ያክላሉ።

አቶ በቀለ ገርባ፡ የኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ-መንበር

ዋናው ማን ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል ሳይሆን በምን ፖሊሲዎችና በምን ርዕዮተ-ዓለም ዙሪያ ነው ሀገሪቱ የምትመራው የሚለውን መመልከት ነው። ያንን የምናይ ከሆነ ከበፊቱ ምንም የተለየ ለውጥ ይመጣል ብለን አናስብም። ነገር ግን ግለሰቦችም የራሳቸው ሚና እንደሚኖራቸው ይታወቃል ።

ስለዚህ አሁን የኢህአዴግ ሊቀ-መንበር የሆኑት እና ነገ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆኑት ግለሰብ ጦር ሠራዊቱንና ደህንነቱን ምን ያህል ይቆጣጠሩታል? የሚለውን እና እነዚህ ተቋማት ሕገ-መንግሥቱ ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው ከፖለቲካ ነፃ ሆነው አመራር እንደሚቀበሉ፣ ምን ያህል ለሕገ-መንግሥቱ ታማኝ እንደሚሆኑ፣ በዚያው ልክም ደግሞ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ያላቸው ታዛዥነት እንዴት እንደሚሆን፤ የሀገሪቱን የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስን ይመስለኛል ይላሉ።

የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊ ነው ብለን አናምንም ይልቁኑም ከታወጀ በኋላ መፍትሔ ሳይሆን የተለያየ ህዝባዊ ተቃውሞ ሲገጥመው እና ሁከት ሲፈጠር ነበር። ስለዚህ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር መሾም በኋላ ይህንን አዋጅ ማንሳት የሚችሉ ከሆነ እንደ አንድ ትልቅ መነሻ ይሆናል ብለን ነው የምንገምተው።

አቶ ጃዋር ሞሃመድ፡ አክቲቪስትና የኦሮሞ ሚዲያ ኔትውርክ ዳይሬክተር

በኦሮሚያ ደረጃ የታዩ ለውጦች ወደ ፌደራል ይሸጋጋራሉ የሚል ተስፋ አለኝ። በተጨባጭ ግን ምን ለውጥ ይመጣል የሚለውን በጊዜ ሂደት የሚታይ ነው።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በኢህአዴግ ባህልና መመሪያዎች ሳይያዝ ሕገ-መንግሥቱ የሚሰጠውን ስልጣን ሳይጨምርና ሳይቀንስ ከተጠቀመበት ለውጥ ለማምጣት አይቸግረውም።

ስለዚህ በሕገ-መንግሥቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው ስልጣንን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስለሚገድበው ተመራጩ ስራውን በአግባቡ እንዲሰራ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በቀዳሚነት ማንሳት አለበት።

በተጨማሪም ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ወደ ዲሞክራሲ ስለሚደረገው ሽግግር መደራደርና የቀሩ እንዲሁም አሁንም የታሰሩ እስረኞችን መፍታት ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው።

የሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ

ሃገሪቱ ካለችበት ሁኔታ አንፃር የዶክተር አብይ መመረጥ ጥሩ ነገር ነው ብዬ አስባለሁ። በሃገሪቱ ውስጥ የተከሰቱትን ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ይፈቱታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያነሱ፣ የተቋረጠው ኢንተርኔት ሙሉ አገልግሎት እንዲሰጥና በህዝቡ መካከል የአንድነት መንፈስ እንዲጠናከር እንዲያደርጉ እፈልጋለሁ።

አቶ መሃመድ አሊ፡ የወልዲያ ከተማ ነዋሪ

በአማራ እና ኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች በነበሩ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ገብተን ነበር። በአፋር እና እዚህ ወልዲያ የሚገኙ ጓደኞቼም ሆኑ እራሴ ቀድመውንም ቢሆን የዶ/ር አቢይን መመረጥ በጉጉት እንጠብቀው ነበር ።

በቅድሚያ የሀገሪቱ ሰላም ወደ ነበረበት እንዲመለስ ሌላው ደግሞ ኢትዮጵያዊ አንድነትን አንግበው ሀገሪቱን ወደፊት ያራምዷታል የሚል ተስፋ አለኝ።

አቶ መብራቱ ዱባለ፡ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ

የዶ/ር አቢይ አህመድ መመረጥ በኢትዮጵያ የተጀመረውን የመልካም አስተዳደር ሥራ የዲሞክራሲ እና የልማት ጥያቄዎችን በየደረጃው ይፈታል የሚል እምነት አለኝ።

በተለይ ደግሞ ወጣት ከመሆናቸው አንፃር ወጣቱን ትውልድ የመረዳት አቅም ይኖራቸዋል ብዬ አምናለሁ። እንዲሁም በየመድረኩ ይነሱ የነበሩ የህዝብ ጥያቄዎችን ይመልሳሉም የሚል ፅኑ እምነት አለኝ።

ተያያዥ ርዕሶች