ሚጉና ሚጉና፡ በኬንያ የተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ የሚታወቁት ግለሰብ በድጋሚ ከአገር እንዲወጡ ተደረገ

ሚጉና በአየር ማረፊያው እንዳይገቡ ከታገዱ በኋላ መታወቂያቸውን ከመስታወቱ ባሻገር ላሉ ሲያሳዩ Image copyright EPA
አጭር የምስል መግለጫ ሚጉና በሳምንቱ መጀመሪያ በድጋሚ ወደ ኬንያ ለመግባት ያደረጉት ጥረት አልተሳካም

በኬንያ ፖለቲካ ውስጥ መንግሥትን በመቃወም የሚታወቁት ሚጉና ሚጉና ከሚኖሩበት ሀገር ካናዳ ወደ ኬንያ ሊገቡ ሲሉ በተነሳባቸው የዜግነት ጥያቄ ምክንያት በአየር ማረፊያ ታግተው ቆይተው በድጋሚ ወደመጡበት እንዲመለሱ ተደርጓል።

ወደ መጡበት ሀገር እንዲመለሱ የተደረገው ጉዳያቸው ፍርድ ቤት ቀርቦ መግባት እንደሚችሉ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ነው።

ረቡዕ እለት የኬንያ ፍርድ ቤት ከፍተኛ የሀገሪቱን ባለስልጣናት ችሎቱ የሰጠውን ይግቡ የሚል ትዕዛዝ ማስፈፀም ባለመቻላቸው ፍርድ ቤት በመድፈር ከሷቸዋል።

የሚጉና ጠበቆች እንደገለፁት ከሆነ ከሰኞ ጀምሮ ታግተው ከቆዩበት አየር ማረፊያ በኤሚሬትስ አውሮፕላን የናይሮቢ አየር ማረፊያን ለቀው ወጥተዋል።

ወደ ዱባይ እንደበረሩም ለማወቅ ተችሏል።

በሰላ ትችታቸው የሚታወቁት እና ጠበቃ የሆኑት ተቃዋሚው ሚጉና፤ ባለፈው ወር ከሀገር እንዲወጡ ሲደረግ ወደ ከካናዳ ነበር የሄዱት።

የኬንያ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛ ጆርጅ ኦዱንጋ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩን፣ የፖሊስ አዛዡን እና የኢሚግሬሽን ሃላፊውን ይለቀቁ የሚለውን የችሎቱን ውሳኔ የማያከብሩ ከሆነ ፍርድ ቤት በመድፈር እንደሚጠየቁ ገልፀውላቸው ነበር።

እነርሱ ግን ሚጉና የካናዳ እንጂ የኬንያ ዜግነታቸውን የሚያሳይ ምንም ሰነድ አለመያዛቸውን በመጥቀስ ተከራክረዋል።

የኬንያ ባለስልጣናት ከዚህ ቀደም ግለሰቡን ሀገር ለቀው እንዲወጡ ያደረጉት የተቃዋሚው መሪ ራይላ ኦዲንጋ ራሳቸውን "የሕዝብ ፕሬዝዳንት" በማለት ቃለ-መሃላ ሲፈፅሙ ተገኝተው በማስፈፀማቸው ነው።

ኦዲንጋ ባለፈው ዓመት በነሐሴ ወር በተካሄደው ምርጫ መሸነፋቸው ይታወሳል።

በኋላም በፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት በምርጫው ሂደት ላይ ክፍተቶች ነበሩ ተብሎ ድጋሚ ምርጫ ሲካሄድ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ያጭበረብራሉ በማለት በድጋሚ ለመወዳደር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ሁለቱ የፖለቲካ መሪዎች ባልተጠበቀ መልኩ በቴሌቪዥን በጋራ ቀርበው ከድህረ ምርጫ ቀውሱ በኋላ የእርቅ ሂደቱን ለመጀመር ቃል ገብተዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ