ቬንዙዌላ ውስጥ ፖሊስ ጣቢያ ላይ በተነሳ እሳት 68 ታሳሪዎች ሞቱ

የታሳሪ ቤተሰቦች Image copyright Reuters

ቫሌንሺያ በተባለችው የቬንዙዌላ ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ ፖሊስ ጣቢያ ላይ እስረኞች ባስነሱት ብጥብጥና እሳት 68 ሰዎች መሞታቸውን ባለስልጣናት ተናገሩ።

የሀገሪቱ ዋና አቃቤ ሕግ ታሬክ ሳአብ ስለክስተቱ ለማወቅ በአስቸኳይ ምርመራ እንደሚጀመር ተናግረዋል።

በእስር ቤቱ ውስጥ እሳቱ የተነሳው ለማምለጥ የሞከሩ ታሳሪዎች ረቡዕ እለት ፍራሾችን በማቃጠላቸው እነደሆነ ተዘግቧል።

የእሳት አደጋው መከሰቱ ከተሰማ በኋላ ፖሊስ ጣቢያውን የከበቡ የታሳሪዎች ቤተሰቦችን ለመበተን ፖሊስ አስለቃስ ጭስ ተጠቅሟል።

አሁን በቁጥጥር ስር የዋለው እሳት አደጋ ከተከሰተ በኋላ አንድ የፖሊስ መኮንን በጥይት መመታቱን የግዛቲቱ ባለስልጣን የሆኑት ጂሰስ ሳንታንደር አረጋግጠዋል።

ባለስልጣኑ ጨምረው እንደተናገሩት ከአደጋው መከሰት በኋላ ከተማዋ የምትገኝበት የካራቦቦ ግዛት በሃዘን ላይ ነች።

የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች እንዳሉት አብዛኞቹ እስረኞች በጭስ ታፍነው እንደሞቱ ተናግረዋል።

ከሟቾቹ መካከልም ታሳሪዎችን ለመጠየቅ ፖሊስ ጣቢያው ውስጥ የነበሩ ሴቶችና ህፃናት እንደሚገኙበትም ተነግሯል። የቬንዙዌላ እስር ቤቶች በእስረኞች የተጨናነቁ ከመሆናቸውም በላይ ግጭቶችና አደገኛ አመፆች በተደጋጋሚ ይከሰቱባቸዋል።

ሃገሪቱ ከገባችበት የኢኮኖሚ ቀውስ አንፃር እስረኞችን በአግባቡ ለመያዝ እየተቸገረች ሲሆን፤ በእስር ቤቶች ያለውን መጨናነቅ ለመቀነስም የተፈረደባቸው እስረኞችን አሁን የእሳት አደጋ እንዳጋጠመው ባሉ ፖሊስ ጣቢያዎቸ ውስጥ ሳይቀር ለማቆየት ተገደዋል።

ጉዳዩን የሚከታተሉ ሰዎች እንደሚናገሩት አንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎች መያዝ ከሚገባቸው እስረኛ አምስት እጥፍ በላይ ታሳሪዎችን እያስተናገዱ ነው።

ባለፈው ወር በካራቦቦ ግዛት የተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ እስረኞች በቀሰቀሱት አመፅ ታሳሪዎችንና የእስር ቤት ጠባቂዎችን አግተው እንደነበር ይታወሳል።

ተያያዥ ርዕሶች