ሩሲያ የአሜሪካን እርምጃ ተከትሎ 60 ዲፕሎማቶችን ከሀገሯ እንዲወጡ አደረገች

በሴይንት ፒትስበርግ የሚገኘው የአሜሪካ ቆንፅላ Image copyright EPA
አጭር የምስል መግለጫ በሴይንት ፒትስበርግ የሚገኘው የአሜሪካ ቆንፅላ ሊዘጋ ነው

ሩሲያ እንግሊዝ ውስጥ የቀድሞ የሩሲያ ሰላይ መመረዙን ተከትሎ አሜሪካ ለወሰደችው እርምጃ አፀፋ ይሆን ዘንድ 60 የአሜሪካ ዲፕሎማቶችን ከሀገሯ እንዲወጡ ያደረገች ሲሆን በሴይንት ፒትስበርግ የሚገኘውን ቆንስላም ዘግታለች።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዳሉት ሩሲያዊያንን ከሀገራቸው ያስወጡ ሀገራት ሁሉ "ተመጣጣኝ" የሆነ ምላሽ ይጠብቃቸዋል።

ይህ እርምጃ የመጣው በደቡባዊ እንግሊዝ ይኖር የነበረ የሩሲያ የቀድሞ ሰላይ እና ልጁ ነርቭን በሚጎዳ መርዝ መመረዛቸውን ተከትሎ ነው።

ዋይት ሀውስ ይህ የሩሲያ ዲፕሎማቶችን ከሀገሯ የማስወጣት ድርጊት "ያልተጠበቀ አይደለም" ሲል ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።

መግለጫው አክሎም "በአሜሪካና በሩሲያ መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ እንዲሸክር ያደርገዋል" ብሏል።

ሰርጌይ ስክሪፓል እና ሴት ልጁ በሚኖሩበት ሳልስበሪ ራሳቸውን ስተው የተገኙት በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ነበር። የእንግሊዝ መንግሥትም ለጥቃቱ ሩሲያን ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ ማድረጉ ይታወሳል።

ሩሲያ የቀድሞ ሰላይዋ መመረዝ ላይ እጇ እንደሌለበት አጥብቃ አስተባብላለች።

የቀድሞ ሰላዩ ስክሪፓል የጤንነት ሁኔታ አሳሳቢ ቢሆንም የልጁ ጤንነት ግን መሻሻል ማሳየቱ ተገልጧል።

ከ20 በላይ ሀገራት ከእንግሊዝ ጎን በመቆም በየሀገራቸው የሚገኙ የሩሲያ ዲፕሎማቶችን ያስወጡ መሆኑ ይታወቃል።

ከእነዚህም መካከል አሜሪካ አንዷ ስትሆን ስድሳ የሩሲያ ዲፕሎማቶችን ከሀገሯ እንዲወጡ አድርጋ፤ በሲያትል የሚገኘው የሩሲያ ቆንስላ ፅህፈት ቤትም እንዲዘጋ አድርጋለች።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ