241 ዓመት የተፈረደበት ጎረምሳ

ቦቢ ቦስቲክ በ2017 Image copyright Missouri Department of Corrections
አጭር የምስል መግለጫ ቦቢ ቦስቲክ በ2017

በሚዙሪ ሁለት ሰዎች ላይ በመተኮስ ዝርፊያ የፈፀመው ጎረምሳ እስከ ህይወቱ ፍፃሜ ድረስ እስርቤት እንዲቆይ ተፈርዶበታል።

ቦቢ ቦስቲክ ምንጊዜም በጣም ማልዶ ነው ከእንቅልፉ የሚነቃው። ፊቱን ታጥቦ፣ ጥርሱን አፅድቶ ቁርሱን ይበላል። ከዛም ሲኤን ኤን አይቶ የማለዳ ፀሎቱን አድርሶ ማንበብ ይጀምራል።

"ማረሚያ ቤቱ አደገኛ ነው። ባለፉት 20 ዓመታት ደግሞ የበለጠ ተበላሽቷል። በዚህ እስር ቤት ችግር እየዳኸም ቢሆን ይፈልግሃል" ይላል ቦስቲክ፤ ስለዚህ አንገቱን ደፍቶ ድምፁን አጥፍቶ መኖርን ምርጫው አድርጓል።

የሕይወት ታሪኮችን ማንበብ ይወዳል፤ የሚፈልገው መፅሃፍ በእስርቤቱ ቤተ-መፃህፍት ውስጥ ከሌለ ቤተሰቦቹ ይልኩለታል። በቅርቡ ያነበበው በዋልተር አይሳክሰን የተፃፈውን "ዘ ኢኖቬተርስ"ን ነው።

ቦስቲክ የቴሌቪዥኑን ድምፅ አጥፍቶ ከስር የሚመጣውን ፅሁፍ ብቻ ያነባል። ድንገት ሰበር ዜና ካለ ብቻ ድምፁን ከፍ ያደርገዋል ካልሆነ ግን ንባቡን ይቀጥላል።

ከምግብ እና ንፋስ መቀበያ ሰዓት በኋላም ወደ ንባቡ ይመለሳል። ሲነጋም የተለመደው የህይወት ዑደቱ ይቀጥላል።

ቦስቲክ በ16 ዓመቱ ነበር 17 ወንጀሎችን በመፈፀም ለተደራራቢ ወንጀሎቹ ተደራራቢ ፍርድ ተሰጠው። ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ካልቀለበሰው በስተቀር እስከ 2091 ድረስ በእስር ላይ ይቆያል።

አሁን 39 ዓመቱ ነው። ፍርዱን ሲያጠናቅቅ ደግሞ 112 አመት ይሞላዋል።

ቦቢ ቦስቲክ አራት ወንድሞች እና እህቶች ያሉት ሲሆን ያለ አባት ነው ያደገው።

"ምሳሌ የሚሆን ወንድ በቤታችን አልነበረም" ይላል "በጎዳናው ላይ እንደፈለኩ ስሆን የሚገስፀኝ ማንም አልነበረም።"

የቦስቲክ ቤተሰቦች በድህነት ስለሚኖሩ በስፖርት ቡድኖች ውስጥ እንኳን ቁምጣ እና ጫማ አሟልቶ መሳተፍ አልቻለም።

10 ዓመት ሲሞላው ማጨስ እና መጠጣት ጀመረ። 12 ዓመት ሲሆነው ዕፅ መጠቀም፣ እድሜው አንድ ዓመት በጨመረ ቁጥር መኪና መስረቅና የተሰረቀ መኪና ማሽከርከር ጀመረ።

"ለእኛ ያ ነበር የኑሮ ደረጃን መግለጫ" ይላል። "ሐብት ማለት የራሳችን ያልሆነን መኪና ማሽከርከርም እንደሆነ ነበር የሚሰማን።"

አንድ ዕለት ግን ሕይወቱ አዲስ ምዕራፍ ጀመረች። ቦስቲክ 16 ዓመት ሞልቶት ነበር። ከሚኖርበት ከተማ ራቅ ብሎ የጓደኛው ጓደኛ የሆነ ልጅ ቤት ሀሽሽ እያጨሱ፣ ጅን እየጠጡ ነበር። ከዚያም የሴት ጓደኛቸው ወደ ደጅ ወጣች።

"በጎረቤት ከሚኖር አንድ ልጅ ጋር እያወራች ነበር" ይላል፤ "መታት፤ እኛን እንደምትጠራን ነገረችው፤ እንድትጠራን ነገራት"

ቦስቲክ እና ጓደኞቹ በስሜት ተሞልተው ወደ ልጁ ሄዱ። "ለዚያ ነው ሽጉጡን የያዝኩት" ይላል።

Image copyright Missouri Department of Corrections
አጭር የምስል መግለጫ ቦቢ ቦስቲክ በ2006

አንድ ጥይት እንኳ ሳይተኮስ ጠቡ በረደ። ቦስቲክ እና ጓደኛው ዶናልድ ሁትሰን ሽጉጡን እንደያዙ ተጨማሪ ሐሺሽ ለማጨስ ሄዱ።

"እያጨስን እያለ አንድ ልጅ አየን፤ የዚያ ሰፈር ልጅ እንዳልሆነ ገብቶናል። በርካታ ነገሮች በመኪው ላይ ጭኗል።"

ልጁ ለተቸገሩ ሰዎች ስጦታ እየሰጠ ሲሆን ሁለት መኪና ሙሉ ስጦታ ነበር። አንደኛው መኪና የገና ዛፍ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ያገለገለ ሶፋ ነው።

"አቅደንበት አልነበረም" ይላል ቦስቲክ ። "አየናቸው፤ ከጓደኛዬ ጋር ተያየን፤ ሁሉም ነገር ቅፅበታዊ ነው ሽጉጤን መዝዤ አወጣሁ።"

ቦስቲክ እና ሁትሰን ወደ መኪናው ተጠጉ። አንድ ልጅ ከመኪናው ላይ ሶፋውን እያወረደች ነበር።

ሽጉጡን ጭንቅላቷ ላይ ደቀኑባት። ለማምለጥ ስትሮጥ ተከተሏት።

ፍቅረኛዋ ስልክ እያነጋገረ ነበር። ሲያያቸው ጮኸባቸው። እርሷን ትተው እርሱን ማባረር ጀመሩ። ተኩሰው ከጣሉት በኋላ መቱት የያዘውንም ገንዘብ እንዲሰጣቸው ጠየቁት።

ገንዘቡን ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ሲቀር ቦስቲክ ተኮሰበት።

"ለምን እንዳደረኩት አላውቅም፣ ልጁን ለመግደል ፈልጌ አልነበረም፣ ላቆስለውም ፈልጌ አልነበረም፣ ማድረግ አልነበረብኝም፣ ይፀፅተኛል... "

ጥይቱ ልጁን መታችው። ከዚያ በኋላ ያለውን 500 ዶላር አውጥቶ ሰጠው። ቦስቲክ እና ሁትሰን ግን አልበቃቸውም።

ስጦታውን በሚሰጡት ቡድን ውስጥ የነበረችውን ሴት የቆዳ ጃኬት ወሰዱ። ከእርሷ ጋር ከነበረውም ሰው ብር ጠየቁ፤ የኪስ ቦርሳውን ወረወረላቸው፤ ተኩሰው መቱት።

ቦስቲክ እና ሁትሰን መጀመሪያ ወደ ነበሩበት ልጅ ቤት ተመለሱ። እዚያ መቆየት እንደማይችሉ ነገረቻቸው።

"ከቤቱ ወጥተን ወደ አንድ ጥግ ሄድን" ይላል ቦስቲክ። ያኔ ነው ሌላ መንገደኛ ያገኙት።

ሴትየዋ ከመኪናዋ ውስጥ የታሸገ ጥቅል እያወጣች ነበር። ቦስቲክ እና ሁትሰን ሽጉጣቸውን ሴትየዋ ጭንቅላት ላይ ደቀኑባት። የመኪናዋን ቁልፍ ተቀብልው እርሷን ከኋላ ካስገቡ በኋላ አስነስተው ሄዱ።

የለበሰችውን ኮት እና የጆሮ ጌጥ እንድታወልቅ አደረጉ፣ ቦርሳዋን ተቀበሏት። ሁትሰን የደበቀችው ብር ይኖራል ብሎ ስለጠረጠረ ጡቶቿን እየነካ ጭምር በረበራት።

ቦስቲክ እና ሁትሰን ጥቂት ከተከራከሩ በኋላ ሴትየዋን ጭር ያለ ስፍራ ጥለዋት ሄዱ። ከአንድ ሰዓት በኋላም በቁጥጥር ስር ዋሉ።

" በፖሊስ እስክያዝ ድረስ የጉዳዩ ክብደት አልታየኝም ነበር" በማለት "ከዛ በኋላ ነው ፀፀት ውስጤን ያኝክ የጀመረው" ይላል።

Image copyright Missouri Department of Corrections
አጭር የምስል መግለጫ ዶናልድ ሁትሰን በ2016። እንደ ሙዚሪ ማረሚያ ቤቶች ድረገፅ ከሆነ ቅፅል ስሙ "ኤኬ-ዲ" እና "ሱሳይድ" ይሰኛል።

ከተያዘ ከአራት ወር በኋላ ቦስቲክ ችሎት ፊት ሳይቀርብ ጥፋቱን እንዲያምን እና 30 ዓመት እንዲታሰር ተነገረው። እስሩ አመክሮም እንዳለው ቢገለፅለት እምቢ አለ።

ከስምንት ወራት በኋላ ደግሞ የችሎቱን ውሳኔ ሰምቶ ዳኛው ለጥፋተኝነቱ የሚሰጡትን እንዲቀበል ተነገረው። እርሱ ግን በእንቢተኝነቱ ፀና።

"አባቴ፣ እንጀራ አባቴ ሌሎችም ይመክሩኛል። አባቴ እስር ቤት ቢሆንም ፃፍኩለትና የማታውቀውን ውሳኔ አትቀበል ምክንያቱም ቀጥሎ ምን ሊመጣ እንደሚችል አታውቅም አለኝ" ስለዚህ ችሎት ፊት ቀርቤ ለመከራከር ወሰንኩ ይላል።

"ጥፋተኛ መሆኔን አውቃለሁ፤ ነገር ግን ሁሌም በችሎት ፊት የተሻለ እድል እንደማገኝ አስብ ነበር። እንደ 17 ዓመት ወጣት በትክክል ማመዛዘን አልቻልኩም።"

ቦስቲክ ፍርድቤት ሲቀርብ በ17 የተለያዩ ወንጀሎቹ ጥፋተኛ ሆኖ ተገኘ። በተጨማሪም በስምንት መሳሪያ ታጥቆ ወንጀል በመስራት ሦስት የዘረፋ ወንጀሎች ጥፋተኛ ተባለ።

በ1997 የጥፋተኝነት ውሳኔው ከመሰጠቱ በፊት ጠበቃው ለዳኛው ደብዳቤ እንዲፅፍ ሃሳብ አቀረበለት፤ ተስማምቶ አራት ጊዜ ፃፈ።

እያንዳንዱ ደብዳቤው ነገሮችን ከማቅለል ይልቅ አባባሱት።

ከሁለት እና ከሦስት ዓመት በፊት የፃፋቸውን ደብዳቤ ሲያነባቸው "መለስ ብዬ ሳያቸው፣ በቂ ፀፀት አላሳየሁም" ይላል ቦስቲክ።

የቦስቲክ እናት ዲያናም ለዳኛው ደብዳቤ ፅፋለች "ከቤተሰቦቼ ከደረሱኝ ውብ ደብዳቤዎች አንዱ ነው፤ ነገር ግን ሊታደገኝ አልቻለም።"

ችሎቱን ያስቻሉት ዳኛ ኢቭሊን ቤከር "ደብዳቤ ፃፍክልኝ፣ እንዴት ያለህ ብልህ ነህ፣ እንዴት ያለኸው ምጡቅ ነህ፣ በዓለም ላይ ካሉ ሁሉ እንደምን የተሻልከው ነህ"

"በዚህ ችሎት ከቆሙት ሁሉ ቂሉ አንተ ሳትሆን አትቀርም። ትንሽ እንኳ ስለጥፋትህ ፀፀት አይሰማህም፤ ከዚያ ይልቅ ስለራስህ ታዝናለህ" በማለት ዳኛዋ ቦስቲክ ላጠፋቸው ጥፋቶች በጥቅሉ ከመቅጣት ይልቅ ለእያንዳንዱ ጥፋቶች ቅጣቱን እንዲቀበል ውሳኔ አስተላለፉ።

"ማረሚያ ቤት ውስጥ ትሞታለህ" አሉት ከውሳኔው በኋላ።

የቦስቲክ ጓደኛ ዶናልድ ሑትሰን ግን የችሎቱን ውሳኔ እቀበላለሁ ብሎ ቀድሞ ስለተስማማ 30 ዓመት ተፈረደበት።

"241 ዓመት ሲፈረድብኝ እውነታው ፍንትው ብሎ ታየኝ፤ እናም እስር ቤት ውስጥ እንደምሞት ነገረችኝ" ይላል ቦስቲክ።

"ይህ ሲሆን ዓለም ተገለባበጠችብኝ፤ እውነታው ገዝፎ ታየኝ፤ ሕይወቴ ተወስዷል። የማንቂያው ደወል የተሰማኝ ከዚህ በኋላ ነበር።"

ቦስቲክ በ14 እና በ15 ዓመቱ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ጀምሮ ቢያቋረጥም ሁለት እና ሦስት ዓመት እስር ቤት ካሳለፈ በኋላ ማንበብ ጀመረ።

መጀመሪያ አንብቦ የተመሰጠበት የማልኮም ኤክስ ግለ ታሪክን ነው። "እኔ ባለፍኩበት ያለፈ ግለሰብ ነው" ይላል ከዚያ በኋላ በመፅሃፍ ላይ መፅሃፍ፣ በንባብ ላይ ንባብ ሆነ።

ትምህርቱን አጠናቀቀ ከዚያም መጽሀፍ መጻፍ ጀመረ። አራት ኢ-ልቦለዶች እና ስምንት የግጥም መጽሐፍትን ጻፈ።

የተለያዩ አጫጭር ስልጠናዎችን መውሰድ ጀመረ። ከወሰዳቸው ስልጠናዎች መካከል አንዱ የተበዳዮች መብት አቀንቃኝ ይሰኛል።

"ከወንጀሉ መፈፀም ጀምሮ እስከ ፍፃሜ ድረስ ያለውን እና ተበዳዮች የሚያልፉበትን ያሳያል" ይላል ቦስቲክ።

"ወንጀሉን ስፈፅም የበደልኳቸው ሰዎች እነማን እንደሆኑ አላሰብኩም ወይም ደግሞ ምን እንዳደረጉኝ አላሰብኩም። ስልጠናው የተበዳዮቹን ወገን እንዳይ አድረጎኛል። ስሜታቸውን እንድረዳ እና እነሱም መብት ያላቸው ሰዎች መሆናቸውን አሳይቶኛል። "

"ስለሚያልፉበት የስሜት ስብራት፣ ከዚያም እንዴት እንደሚያገግሙ መርዳት እንደሚቻል ተምሬያለሁ። እኔ ያደርስኩባቸው ነገር ስሜታቸው እንዲሰበር በማድረጉ እና ተበዳዮችን ራሴ ስለፈጠርኳቸው ይህንን የማደርገው ከልቤ ነው።"

ቦስቲክ ዲግሪውን ለማግኘት መውሰድ ያለበት ክፍሎች አሉ።

"ግድ የለሽነት የእስር ቤቱ ህግ ነው" ይላል። "ወጣቶቹ ተኝተው ነው የሚውሉት። አያነቡም፣ አያጠኑም፣ እኔ እስር ቤት በገባሁበት ወቅት እናነብ ነበር አሁን ግን ቴሌቪዥንና ጨዋታ ብቻ ነው። ሁሉ ነገር ጨዋታ ሆኗል።"

ቦስቲክ በትምህርት ያምናል።ወደፊት ክህሎቱን ተጠቅሞ እርሱ እየሰረቀ ይኖር የነበረበት ጎዳና ላይ የሚገኙ ህፃናትን መርዳት ይፈልጋል። መጀመሪያ ግን ከእስር ቤት መውጣት ይኖርበታል።

Image copyright ACLU

ለ25 ዓመት በዳኝነት አገልግላ ጡረታ የወጣችው የ69 ዓመቷ ቤከር፤ ቦስቲክን በደንብ ታስታውሰዋለች። የፃፋቸውንም ደብዳቤዎች ጨምሮ።

በሥራ ዘመኗ ከሰጠችው ውሳኔዎች ሁሉ ይህ የቦስቲክ 241 ዓመት የእስር ቅጣት ትልቁ ነው።

"መለስ ብዬ ሳስታውሰው በወቅቱ ቦቢን ለአካለ መጠን እንደደረሰ፣ እንደ አዋቂ ሰው ነበር ያየሁት ያም ስህተት ነበር" ትላለች።

30 ዓመት ብቻ ቢታሰር ይበቃው ነበር ስትልም ትናገራለች። ያ ሆኖ ቢሆን ከአመክሮ ጋር ቦስቲክ በዚህ ዓመት ከእስር ይወጣ ነበር ማለት ነው።

"ስለ ቦቢ እንዳነበብኩት ከሆነ አሁን ያኔ የቅጣት ውሳኔዬን ያስተላለፍኩበት የ16 ዓመት ልጅ አይደለም። በርካታ በጎ ተግባሮችን እያከናወነ ነው" ትላለች።

ቦስቲክ ለበደላቸው ግለሰቦች የይቅርታ ደብዳቤ ለመፃፍ ከ10 ዓመት በላይ ፈጅቶበታል። ምንም ምላሽም አልሰጡትም።

በመገናኛ ብዙሃንም ላይ ቀርቦ ይቅርታ ጠይቋል።

"የበደልኳቸው ግለሰቦች በእስር ቤት ውስጥ እንድሞት የሚፈልጉ ከሆነ ውሳኔያቸውን አከብራለሁ።"

የአሜሪካው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሚቀጥለው ወር የቦስቲክን ጉዳይ ለማየት ይሰየማል። የሕግ ክርክር የሚነሳበት ቢሆንም የረዥም ጊዜ ፍርደኛው ቦስቲክ ሊለቀቅ ይችላል።

ቦስቲክ ዛሬም ተስፋ ያደርጋል "ነፃነት አእምሮህን ለቆ አይሄድም፣ እዚህ እስር ቤት ቴሌቪዥን ስታይ፣ ወጥተህ አየር ስትቀበል፣ ነፃነት እንደሌለህ ታስባለህ፤ ስለዚህ ሁሌም ትመኘዋለህ" ይላል።

ተያያዥ ርዕሶች