ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚጠበቁ 10 ነገሮች

የፎቶው ባለመብት, OPDO Official
የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ዶ/ር አብይ አህመድ
ኢትዮጵያ ለሦስት ዓመታት ያህል በሕዝባዊ ተቃውሞዎች ስትናጥ ቆይታለች። እነዚህ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ለመግታት ገዢው ፓርቲ ከኃይል በተጨማሪ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱ ይታወሳል።
ከእነዚህም መካከል የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን፣ ጋዜጠኞችን እና ጦማሪዎችን ከእስር መፍታት ይገኝበታል። ነገር ግን ተቃውሞዎች ሊቆሙ ስላልቻሉ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከፓርቲውም ከመንግሥት ስልጣን ለቀዋል።
አዲሱ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን የመጡት ሀገሪቷ በርካታ ፈተናዎችን በተጋፈጠችበት ወቅት ነው። በዚህ ወቅት ከእርሳቸውም ሆነ ከፓርቲያቸው የተለየዩ ነገሮችን እንደሚጠብቁ ያነጋገርናቸው የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እና የድሬዳዋ፣ ሀዋሳ፣ ወልዲያ፣ሀሮማያ እና አፋር ነዋሪዎች ነግረውናል።
1. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳት
በኢትዮጵያ ከተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ በኋላ በተለያዩ ስፍራዎች የሰው እና የንብረት ውድመቶች ገጥመዋል። ይህንን ተከትሎም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ሲሆን ሁኔታዎች የተረጋጉ ሲመስሉ አዋጁ ተነስቷል።
ነገር ግን በቅርቡ በድጋሚ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተደንግጓል። ይህንን ተከትሎም የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ የተቀዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ የውጭ ሀገራት ኢምባሲዎች በአዋጁ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ በይፋ ገልፀዋል።
እኛም ያነጋገርናቸው ምሁራን እና ፖለቲከኞች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊ ነው ብለው አያምኑም። አዋጁ ከተደነገገ በኋላም ለሐገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን ሳይሆን ሁከት ሲፈጠር እና ሰዎች ሲሞቱም ታይቷል የሚሉት እነዚህ አካላት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከተሾሙ በኋላ የመጀመሪያ ሥራቸው ይህንን አዋጅ ማንሳት እንዲሆን ይጠይቃሉ።
ለዚህ ደግሞ እንደመከራከሪያ ካቀረቧቸው መካከል አንዱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው ስልጣንን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስለሚገድበው ተመራጩ ሥራውን በአግባቡ እንዲሰራ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በቀዳሚነት ማንሳት አለበት የሚልም ይገኝበታል።
2. የፍትሕ ሥርዓቱን ማሻሻል
በኢትዮጵያ ውስጥ የሕግ የበላይነት ሰፍኖ ለማየት በህግ ፊት ሁሉም አካላት እኩል መሆናቸው መረጋገጥ አለበት የሚሉት ምሁራኑና ፖለቲከኞቹ ለዚህ ደግሞ ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ፣ ማረሚያ ቤት እንዲሁም ሌሎች የፍትህ ሥርዓቱ አካላት ሕጉን እና ሕገ-መንግስቱን ብቻ ተከትለው እንዲሰሩ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ይመክራሉ።
እነዚህ አካላት ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሚጠብቁት ነገር መካከል አንዱ የፍትህ ሥርዓቱን እንዲያሻሽሉ ነው። በተለይ ደግሞ ፍርድ ቤቶች ራሳቸውን ችለው ያለምንም ጫና ውሳኔ መስጠት የሚችሉበትን አቅም መፍጠር እንዳለባቸው ያምናሉ።
3. ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይትና ድርድር ማድረግ
የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ለ17 ቀናት ካደረገው ስብሰባ በኋላ ካስቀመጣቸው ነጥቦች መካከል አንዱ ለተሻለ ሀገራዊ መግባባትና የተረጋጋ ሰላማዊ የፖለቲካ ሥርዓት በሰላማዊ መንገድ ከሚንቀሳቀሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለውይይትና ለድርድር መቀመጥን ነው።
ስለዚህ ውይይትና ድርድር ተካሂዶ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በሀገራችን እንዲኖር ማድረግ ሀገሪቱ ዳግመኛ እንዲህ አይነት የፖለቲካ አዙሪት ውስጥ እንዳትገባ እንደሚያደርጋት በፅኑ ያምናሉ። ወደ ዲሞክራሲ ለሚደረገው ሽግግር መደራደርና ሰጥቶ በመቀበል ላይ የተመሰረተ ሥርዓት መዘርጋት ወሳኝ መሆኑንም ያሰምሩበታል።
4. የፖለቲካና የህሊና እስረኞችን መፍታት
በኢትዮጵያ ውስጥ በተቃውሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላትና አመራሮች፣ በጋዜጠኞች፣ ጦማሪዎችና ሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ላይ እስርና እንግልት ሲደርስ በተደጋጋሚ ተስተውሏል ይላሉ ያነጋገርናቸው የሰብአዊ መበብት ተሟጋቾች። ከእስር ያመለጡ በርካቶች ደግሞ በሃገር ውስጥ የሚፈፀምባቸውን ጥቃት በመሸሽ በስደት በህይወት መቆየትን መርጠዋል ሲሉም ያክላሉ።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና ምሁራን እንደ ፀረ ሽብር ያሉ ሕጎች ከወጡ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብአዊ መብቶች አያያዝና ለሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች እየጠበበ ስለመጣው የመንቀሳቀሻ ስፍራም ያስረዳሉ።
ስለዚህ የፖለቲከኞችና የህሊና እስረኞችን ሙሉ በሙሉ መፍታት ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስተር ከሚጠብቋቸው ሥራዎች መካከል ይገኙበታል።
5. የሰብአዊና የዲሞክራሲ መብቶችን ማሻሻል
ምሁራኑ በሀገሪቱ ውስጥ ለተከታታይ ዓመታት በዘለቀው ሕዝባዊ ተቃውሞ ውስጥ እንደተስተዋለው የሰብአዊ መብቶችና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ጥያቄዎች ሲቀርቡ ነበር ይላሉ።
ተሿሚው ጠቅላይ ሚኒስትር በሕዝቡ ዘንድ ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ቃል የሚገቡ ከሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የሲቪል ማሕበረሰብ ቷቋማት በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት እንዲሁም ሃሳብ በነፃነት የሚንሸራሸርበት መድረክ ማግኘትን የሚደግፉ የህገ-መንግስቱ አንቀፆች የሚከበሩበት ምህዳር እንዲፈጠር ማድረግ ትልቁ የቤት ሥራቸው ይሆናል ብለው ያስባሉ።
6. በጦር ሠራዊቱ እና በደህንነቱ ውስጥ ተጠያቂነትን ማስፈን
ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ምሁራን የጦር ሠራዊቱና የደህንነት ተቋማት ለህገ-መንግሥቱ እንዲሁም ለፓርላማ አባላት ያላቸው ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እንዲሁም የሃገሪቱ የበላይ ህግ የሆነው ህገ-መንግሥት እንደሚያዘው በእነዚህ ተቋማት ወስጥ ያለውን የብሄር ተዋፅኦን ተመጣጣኝ ማድረግ አስፈላጊም እንዲሁም አስቸኳይ የቤት ሥራ ነው ይላሉ።
7.ሕገ-መንግስቱን ማክበር፤ ማስከበር
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በኢህአዴግ ባህልና መመሪያዎች ሳይያዝ ሕገ-መንግሥቱ የሚሰጠውን ስልጣን ሳይጨምርና ሳይቀንስ ከተጠቀመበት ለውጥ ለማምጣት አይቸግረውም የሚሉት ምሁራን እና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የፌደራል እና የክልሎችን ስልጣን በሚመለከት፣ የፍትህ ሥርዓቱን ለማስተካከል፣ የሰብአዊ መብቶችን ለማክበርም ሆኑ ለሌሎች ጉዳዮች ሕገ መንግስቱን ማክበርና ማስከበር ላይ እንዲያተኩሩ ያሳስባሉ።
በተጨማሪም ሀገሪቱን ማረጋጋት፣ የምትመራበት ፌደራላዊ ሥርዓት ለብዙ ችግር የዳረጋት ከመሆኑ አንፃር እሱን ማስተካከልም ከሥራቸው መካከል እንደሚገኝበት ያስታውሳሉ።
8. የምሁራንን ተሳትፎ ማሳደግ
ዶ/ር አቢይ ከተማረው ወገን በመሆናቸው ምሁራንን በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ ያደርጋሉ ብለው የሚያምኑት ደግሞ ምሁራን ናቸው።
በፖለቲካዊ ተሳትፎ ውስጥ የማይታወቁ ምሁራንን በካቢኔያቸው ውስጥ እና ከዚያም ውጭ በማሳተፍ በጋራ መስራት ያስፈልጋል የሚሉት ምሁራኑ፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሥራቸውን ሲጀምሩ በሚፈፅሙት ቃለ-መሃላ እና በሚወስዷቸው እርምጃዎች ይህን እናያለን ብለው ይጠብቃሉ።
9. ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ ከፍ ማድረግ
በተጨማሪም ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶችንና የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠናን የሚይዙበት መንገድ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቃት መፈተኛዎች መሆናቸውንም ምሁራኑ ያስረዳሉ።
በቀጣይም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢትዮጵያ በተለያዩ ሃገራት ያላትን የሰላምና ደህንነት የማረጋጋት ሥራን ቀጣይነት ማረጋገጥ እንደሚጠበቅ፣ በቀጠናው ያላት ተሰሚነት ቀጣይነት እንዲኖረው መስራትም ያስፈልጋቸዋል ባይ ናቸው።
10. ለወጣቶች የሥራ እድልን ማስፋት
በተለያዩ የሃገሪቱ ከተሞች የሚኖሩ ወጣቶች እንደሚናገሩት ዶ/ር አቢይ አህመድ ለወጣቶች ትኩረት ይሰጣሉ በማለት ተስፋ ያደርጋሉ። በሀገሪቱ ያለውን ሥራ አጥነትን ለማስተካከል እርምጃ ይወስዳሉ ብለውም ይጠብቃሉ።
ያለውን የሥራ አጥነት ለማስተካከልም የተለያዩ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች እንዲወሰድ የሚጠብቁት እነዚህ ወጣቶች፤ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የእኩል ተጠቃሚነት፣ ሰላም እና መረጋጋትን ማስተካከል ከቻሉ ሥራ አጥነቱ በቀላሉ ይቀረፋል ባይ ናቸው።