ታግተው የነበሩት የትሪፖሊ ከንቲባ ተለቀቁ

ከንቲባው Image copyright AFP/GETTY

የሊቢያዋ መዲና ትሪፖሊ ከንቲባ ለሰዓታት በታጣቂዎች ታግተው ከቆዩ በኋላ መለቀቃቸውን ቤተሰቦቻቸው አሳወቁ።

አብደልራውፍ ቢይተልማል ከቤታቸው በታጣቂዎች የተወሰዱት ትናንት ሃሙስ ጠዋት ላይ ነበር። ቤተሰቦቻቸው እንዳረጋገጡት ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ነው የተለቀቁት።

ለከንቲባው ቤተሰብ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ታጣቂዎቹ ወደመኖሪያቸው ሲመጡ ጥይት መተኮሳቸውንና የከንቲባውን ወንድ ልጅ እንደመቱት ተናግረዋል።

ቢሆንም ግን በሀገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ-ሕግ መስሪያ ቤት ውስጥ የምርመራ ክፍል ሃላፊ የሆኑ ግለሰብ ከንቲባው ለጥያቄ ወደ እስር ቤት እንደተወሰዱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ነገር ግን ባለስልጣኑ ሳዲቅ አልሱር ከንቲባው በቁጥጥር ስር የዋሉት በሕጋዊ መንገድ ስለመሆኑ ምክንያት አልሰጡም።

የትሪፖሊ ከተማ ከንቲባን ለመያዝ ከዕኩለ ሌሊት በኋላ ወደቤታቸው የሄዱት ታጣቂዎች ጥይት መተኮሳቸውን የከንቲባው ቤተሰብ ምንጮች ተናግረዋል።

ሐሙስ ዕለት የከንቲባው በታጣቂዎች መያዝን በመቃወም የዋና ከተማዋ ምክር ቤት ሥራውን አቁሞ ነበር።

በሊቢያ ያሉ ታጣቂ ቡድኖች በመንግሥት ባለስልጣናትና ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት በመፈፀምና በማስፈራራት ይታወቃሉ።

በሊቢያ በታጣቂዎችና በመንግሥት ኃይሎች የሚፈፀሙ ሰዎችን በቁጥጥር ስር የማዋል ድርጊቶች የተደበላለቁ በመሆናቸው ሕጋዊውን ከሕገ-ወጡ ለይቶ ለማወቅ አስቸጋሪ እንደሆነ ይነገራል።

ለአስርታት ሃገሪቱን የመሩት ሙአመር ጋዳፊ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ቀውስ ውስጥ በገባችው ሊቢያ፤ የመንግሥት ኃይሎችና ታጣቂዎች የሃገሪቱን ሥልጣን ለመቆጣጠር ፍልሚያ ከጀመሩ ሰባት ዓመት ሆኗቸዋል።

ተያያዥ ርዕሶች