ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ለኤርትራ መንግሥት የሰላም ስምምነት ጥሪ አቀረቡ

ዶክተር አብይ አህመድና ኃይለማርያም ደሳለኝ

የፎቶው ባለመብት, EBC

ዛሬ መጋቢት 24 2010 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር አብይ አህመድ መንግስት ከኤርትራ መንግስት ጋር ለዓመታት የዘለቀው አለመግባባት እንዲያበቃ እንደሚፈልግ ገልፀዋል።

ጊዜው የአፍሪካ ቀንድ በተለያዩ ሃይሎች ፍላጎት ከመቼውም በላይ ውስብስብ መጠላለፍ ውስጥ እንዳለ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በባህል፣በቋንቋና በታሪክ የተሳሰሩት ሁለቱ አገራት ወደ ስምምነት ሊመጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

"በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለቱ አገራት ህዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል ልዩነቶቻችንን በውይይት ለመፍታት ያለንን ዝግጁነት እየገለፅኩ የኤርትራ መንግስትም ተመሳሳይ አቋም እንዲወስድ ጥሪዬን አቀርባለው"ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ ያለውን አለመረጋጋት በማስመልከት ሲናገሩ ለደረሰው ጥፋት ህዝብን ይቅርታ በመጠየቅ ለችግሩ እልባት በመስጠትም ህዝቡን እንደሚክሱ ቃል ገብተዋል።

ህዝቡ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሃሳቡን መግለፅ እንዳለበት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ በተመሳሳይ መንግስትም ህግን የማክበርና የማስከበር ግዴታ እንዳለበት ጠቁመዋል።

ህዝቡ ብሄርን፣ሃይማኖትንና ሌሎች ልዩነቶችን መሰረት በማድረግ ከበደል ጋር ሳይሆን ከፍትህ ጋር በመተባበር የተሻለ ነገን መፍጠር ላይ ማተኮር እንዳለበትም ተናግረዋል።

አገሪቱን ከፈተኗት ዋና ነገሮች መካከል የወጪ ንግድ የተፈለገውን ያህል አለማደግ አንዱ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በዚህም የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የዋጋ ንረትና ኑሮ ውድነት ህዝቡን እንደተጫኑትና መንግስትም የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ሙስና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌላ ያነሱት የአገሪቱ ተግዳሮት ነው።የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥና የሴቶችን ተሳትፎ ማስፋትም እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል።

መንግስት ዲሞክራሲን ለማስፈን የተለየ ሃሳብ ያላቸው ተቃዋሚዎች እንደ ተቃዋሚ ሳይሆን እንደ ተፎካካሪ ታይተው በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታን እንደሚያመቻችም አረጋግጠዋል።

እነዚህ ተፎካካሪዎችም በዚህ ውስጥ ተሳታፊ በመሆን የአገሪቱን እርምጃ እንዲያግዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በንግግራቸው የህዳሴው ግድብ ግንባታ ሰባተኛ ዓመት ላይ እንዳለ የጠቀሱት ዶ/ር አብይ ህዝቡ ከግድቡ ግንባታ ባሻገር ግድቡን ተከትሎ የሚመጣውን የአገሪቱን ብልፅግና መመልከት እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል።

ስልጣናቸውን ያስረከቡት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር በቀጣይነት በሙሉ ልባቸው በስራ እንደሚያግዙ በፅህፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ ገልፀዋል።

ጨምረውም "ህዝብን በማገልገል የሚገኘውን እርካታ አግኝቻለሁ፤ በቀጣይነትም ማንበብ እየተመኘሁ ያላነበብኳቸውን አነባለሁ፤ እፅፋለሁ። እንዲሁም ማገልገል በሚገባኝ ክፍት ቦታ ለኢትዮጵያ እንዲሁም ለአፍሪካ እሰራለሁ" ብለዋል።