ዊኒ ማንዴላ በ81 ዓመታቸው አረፉ

ዊኒ ማንዴላ Image copyright AFP

ደቡብ አፍሪቃዊቷ የፀረ-አፓርታይድ አቀንቃኝ ዊኒ ማዲኪዜላ ማንዴላ በ81 ዓመታቸው ማረፋቸውን ረዳታቸው አስታወቁ።

የአፓርታይድ አገዛዝን በፅኑ በመቃወም የሚታወቁት የኔልሰን ማንዴላ የመጀመሪያ ባለቤት ዊኒ ማንዴላ በጤና እክል ምክንያት ሆስፒታል ይመላለሱ እንደነበር ቃል-አቀባያቸው ቪክቶር ዲላምኒ አሳውቀዋል።

"ዊኒ ከጤና እክል ጋር ትግል ገጥመው ብዙ የታገሉ ሲሆን በስተመጨረሻም ቤተ-ዘመድ በተሰበሰበበት መጋቢት 24 በሰላም አርፈዋል" ሲሉ ቃል-አቀባዩ ተናግረዋል።

ለ38 ዓመታት ያህል ከኔልሰን ማንዴላ ጋር በትዳር የቆዩት ዊኒ ባለቤታቸው ለ27 ዓመታት እስር ላይ በነበሩት ወቅት አፓርታይድን በመታገል ትልቅ እውቅናን ማትረፍ ችለዋል።

በስተኋላም በጊዜው በነበረው የአፓርታይድ አገዛዝ የአምስት ዓመት እስር ተበይኖባቸው እንደነበርም ይታወሳል።

ኋላ ላይ ግን ለበርካቶች የነፃነት ታጋይ ምልክት የሆኑት ዊኒ 'ባንዳዎች' በጎማ መቃጠል አለባቸው ሲሉ ተደምጠዋል ተብለው ተከሰሱ። አልፎም የኤኤንሲ ፓርቲ ሶዌቶ በተሰኘችው የደቡብ አፍሪካ ከተማ የሸብር ጥቃት አሲረዋል ሲል ከሰሳቸው።

ለጥቆም አንድ የ14 ዓመት ታዳጊ መሞት ተጠያቂ ናቸው በሚል ክስ የስድስት ዓመት እስር ተፈረደባቸው። ወንጀሉን አልፈፀምኩም ሲሉ የካዱት ዊኒ ቅጣቱ በዓይነት እንዲሆንላቸው ተደረገ።

ምንም እንኳ ዊኒ ከላይ የተጠቀሱትን ወንጀሎችን ፈፅመዋል ተብለው በኤኤንሲ ፓርቲ ቢወቀሱም ባለቤታቸው ኔልሰን ማንዴላ ግን እሷ ጥፋተኛ አይደለችም ሲሉ ከጎናቸው ቆመዋል።

ዊኒ ማንዴላ በምስራቅ ኬፕ ትራንስኬይ በመባል በምትታወቅ ቦታ ነበር በአውሮፓውያኑ 1936 የተወለዱት።

የማሕበረሰብ ሥራ ላይ ሳሉ ማንዴላን የተዋወቁት ዊኒ ምንም እንኳ ትዳራቸው 1996 ላይ ቢፈርስም ከባለቤታቸው ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ነበራቸው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ