የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር እንዴት ተመለከቱት?

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በፓርላማ ንግግር ሲያደርጉ

የፎቶው ባለመብት, EBC

ትናንት መጋቢት 24 2010 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር አብይ አህመድ የኃገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አስመልክቶ ንግግር አድርገዋል።

ከኤርትራ መንግስት ጋር እርቅ ለመፍጠር ጥሪያቸውን ያቀረቡት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በተለያዩ ተቃውሞዎች ሰበብ ህይወታቸው ለተቀጠፉ ግለሰቦች ይቅርታን መጠየቅ፣ በኃገሪቱ ላይ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎችን እንደ ተፎካካሪ ማየትና ማሳተፍ፤ የጋራ መግባባትና ብሄራዊ እርቅ መኖር አስፈላጊነት በንግግራቸው ከጠቀሷቸው መካከል የተወሰኑት ናቸው።

ይህ ንግግር ብዙዎችን ያስደመመ ሲሆን ብዙዎችም ያላቸውን አስተያየቶች በተለያዩ ሚዲያዎች እየገለፁ ነው።

በቅርቡ ከእስር ቤት የተፈታው የሰማያዊ ፓርቲ አባል አቶ ዮናታን ተስፋየ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር አስመልክቶ "አነሳሽና ተስፋ ሰጭ፤ ቀናና ትህትና የተሞላበት" ንግግር እንደሆነ ያስረዳል።

የንግግራቸውን ዘይቤ ብቻ ሳይሆን ህዝቡ ውስጥ ጠልቀው የነበሩ አንኳር ችግሮችን ንግግራቸው በመንካቱ የብዙዎችን ቀልብ መሳብ እንደቻለም ተናግሯል።

ከነዚህም ውስጥ የመድብለ-ፓርቲ ስርዓት አስፈላጊነት፣ የዲሞክራሲ ግንባታ እንዲሁም በተለያዩ ተቃውሞዎች ምክንያት ህይወታቸው ላጡ ግለሰቦች ይቅርታ መጠያቃቸው በዋነኝነት ያየቸዋል።

ንግግራቸው የመጀመሪያ እርምጃ ነው የሚለው ዮናታን ከዚህ በኋላ የተናገሯቸውን ነገሮች ወደ ተግባር መቀየሩ ዋናው ነገር ነው ብሏል።

" የተለያዩ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት፤ ቀስ በቀስ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎችንም አሳታፊ በሆነ መንገድ ወደ ድርድሩ ሲያመጡ፤ ካቢኔውንም ለኃገር ተቆርቋሪና በሙያ የበቁ ሰዎችን ሲያሰባስቡ ፤ የሚሉትን ነገር የሚኖሩ ሰው ናቸው ማለት እንችላለን" ይላል።

ለትግሉ ህይወትን ጨምሮ ብዙ መስዋዕትነትን እንደተከፈሉ የሚናገሩት አቶ ዮናታን የጋራ መግባባትና ብሔራዊ እርቅ እንደሚያስፈልግ እርሳቸውም መናገራቸው በግሉ የነበረውን ቁስል እንደሻረ እንደሚቆጥረው ይናገራል።

ተሰናባችና መጪ መራሄ መንግስታት በዚህ ደረጃ የስልጣን ሽግግር ሲያደርጉ ማየት አስደናቂ እንደሆነ የሚናገረው የስነ-መለኮት መፅሀፍ ደራሲና ተርጓሚ አቶ ጳውሎስ ፈቃዱ ነው።

ታሪክን አጣቅሶ የሚናገረው አቶ ጳውሎስ ከዚህ ቀደም ስልጣን የሚቆናጠቱት ከኃገር መውጣት ወይም ሌሎች ሁነቶች እንደሚታዩበት ይናገራል።

"ምንም እንኳን በአንድ ፓርቲ ውስጥ ቢሆንም ይህ አስገራሚ ነው" ይላል።

የዶ/ር አብይ አህመድ ንግግርንም አስመልክቶ ሀገሪቱ ከነበረችበት የብሄር ግለትና የመፈራረስ ስጋቶች አንፃር ተስፋን የሚያንሰራራና የአንድነት መንፈስንም የሚያመጣ መሆኑንም ገልጿል።

በባለፉት ንግግሮች ፀረ-አንድነት የሚመስሉ ንግግሮች ሲሰሙ እንደነበርና አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ግን ታሪካዊ ዳራውን ይዘው የተለያዩ ህዝቦች በአንድነት የከፈሉበትን መስዋዕት አስታዋሽ እንደሆነም ይጠቅሳል።

በተለይም በተደጋጋሚ በኢህአዴግ ባለሥልጣናት ዘንድ የሚጠቀሱትን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ስም አለመጠቀሱ " ከሙት መንፈስ የመላቀቅ" ምልክት እንደሆነም ይገልፃል።

በአጠቃላይ ንግግራቸው " አንድነትን ፍቅርን፣ ይቅር መባባልን የሚሰብክ፤ የሞቱ የተጎዱ ግለሰቦችንና ቤተሰቦቻቸውን ይቅርታ መጠየቅ፤ በዛም ሂደት ውስጥ የሞቱ የፀጥታ ሰዎችን አክብሮት መስጠት፤ ሚናቸው የተዘነጉትን እናትና ሚስቶችን ማስታወስ" ያተኮረ እንደሆነ ይናገራል።

ከዚህም በተጨማሪ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በ40ዎቹ እድሜ ላይ የሚገኙ መሆናቸው ለዘመናት የስልጣን ቦታን ተቆናጥጠው የነበሩት የ60ዎቹን ትውልድ በተወሰነ መልኩ የሰበረ መሆኑ ለየት እንደሚያደርገው ተናግሯል።

በሌላ በኩል የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና አቀንቃኞች አባል የሆነው ናትናኤል ፈለቀ ንግግራቸውን ተከትሎ ዲሞክራሲን ለመገንባት የሚያስፈልጉት የዲሞክራሲ ተቋማት፣ ምርጫ ቦርድ ነፃ በሆነ መንገድ ሊቋቋም እንደሚገባ ይናገራል።

ከዚህም በተጨማሪ የደህንነቱና ሰራዊቱን ማሻሻልም ሌላ የሚጠብቃቸው የቤት ስራም እንደሆነ ያስረዳል።

የሰጡትን ንግግር መልካምነቱን አድንቆ በአጭርና በረዥም ጊዜ ሊሰሩትን ያሰቡትን ዕቅድ ቢያሳውቁ መልካም እንደሆነም ለቢቢሲ ገልጿል።

"ኃገሪቷ በአንድ ዓመት ተኩል ውስጥ ሁለተኛ የአስቸኳይ ጊዜን አውጃለች። ይህም በዜጎች ላይ ፍርኃትን ጭኗል እናም ዜጎች የበለጠ ነፃነት እንዲሰማቸው አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳት ያስፈልጋል" ብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ በተለያየ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ምክንያት እስር ቤት ያሉ ግለሰቦች እንዲፈቱ ማድረግ አፋጣኝ ስራም እንደሆነ ናትናኤል ገልጿል።

የቀድሞ ጋዜጠኛና የኮሚኒኬሽን ባለሙያዋ ቤተልሔም ነጋሽም አስተያየትም ከዚህ የራቀ አይደለም።

"ንግግራቸው የአገር አንድነት ፣አንድላይ መስራት፣ አገርን ከፍ ማድረግንና ስምምነትን የሚሰብክ ነበር ።ንግግራቸው የተለየ ስሜትን ፈጥሮብኛል።" ትላለች።

በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የስርዓተ-ፆታ የኃይል አሰላለፍ ላይ በመፃፍ የምትታወቀው ቤተልሄም ስለ ሴቶች ተሳትፎ የሰጡት አስተያየት እንደሚያመዝንባትም ትናገራለች።

በኢህአዴግ መንግሥት ሴቶችን ተሳታፊ እንደሆኑና ህጎችም በመሻሻላቸው የሴቶችን ጥያቄ መልሷል የሚለው ኃሳብ እንደሚንፀባረቅ ገልፃ የዶ/ር አብይ ምላሽ ግን ያለውን ክፍተት ያሳየ እንደሆነ ትናገራለች።

"መንግስት ከሴቶች ጋር እስከ ዛሬ ለሰራው ነገር እውቅና ቢሰጡም ካደረግነው ያላደረግነው ይበልጣል ብለዋል በግልፅ።" ትላለች

ከዚህም በተጨማሪ እንደ ትልቅ ነጥብ ያየችው ለዘመናት በባህሉ እውቅና የተነፈገውን የእናትነትና የሚስትነትን እውቅና መለገሳቸውን እንደ ትልቅ ነጥብ እንደምትቆጥረው ትናገራለች።

"የሴቶች ሚና ዋጋ መስጠታቸው እንዲሁም ሚናው ለዘመናት ዋጋ ሳይሰጠው መቅረቱንም መጥቀሳቸው ትልቅ ነገር ነው።ባደባባይ በፓርላማ እናታቸውንና ባለቤታቸውን ማመስገናቸውም ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው። "ትላለች።