ኩዌት ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞችን እንደምትፈልግ አሳወቀች

ከሳኡዲ አረቢያ ተመላሽ ኢትዮጵያውያን

ፊሊፒንስ ዜጎቿ ወደ ገልፍ ባህረ-ሰላጤ እንዳይሄዱ ያዘዘችውን እገዳ ተከትሎ የተከሰተውን እጥረት ለመመሙላት የኩዌት ባለስልጣናት የቤት ሰራተኞችን ከኢትዮጵያ እንደሚወስዱ አስታውቀዋል።

የነዋሪዎች ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት ጄኔራል ታላል አል ማሪፊ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደተናገሩት ሀገሪቷ በሯን ለኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞች ክፍት እንዳደረገችና ይህም በቤት ሰራተኞች እጥረት ያለውን ክፍተት እንደሚሞላና ዋጋውም እንደሚቀንስ ነው።

ፊሊፒንስ ዜጎቿ ለስራ እንዳይሄዱ እገዳ የጣለችው የ29ዓመቷ ጆዋና ዴማፌሊስ ግድያን ተከትሎ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2016 ከጠፋች በኋላ ሬሳዋ በማቀዝቀዣ ውስጥ ተገኝቷል። በሰውነቷም የመሰቃየት ምልክቶች ነበሩ።

ቀጣሪዎቿ ሌባኖሳውያው ወንድና ሶሪያዊ ሴትም በዚህ ሳምንት የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸዋል።

ኢትዮጵያ በበኩሏ በውጭ አገር የሥራ ስምሪት ላይ ለዓመታት ጥላው የነበረውን እገዳ ከጥቂት ወራት በፊት አንስታለች።

በቤት ሰራተኝነት ወደ ተለያዩ አረብ አገራት የሚሄዱ ኢትዮጵያዊያን ላይ በአሰሪዎች መደብደብ፣ መደፈር፣የጉልበት ብዝበዛ ፣ክፍያ መከልከልና ሌሎችም አስከፊ ስቃዮች ወደ አረብ አገራት የሄዱ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እጣ ነበር።

በባለፈውም ዓመት የኩዌት ፖሊስ አንዲት የቤት ሰራተኛ ከሰባተኛ ፎቅ ላይ ልትዘል ስትል የሚያሳይ ቪዲዮን በመቅረጿ በቁጥጥር ስር ውላ ነበር።

የተለያዩ የመብት ተሟጋቾች ኩዌትን ጨምሮ በተለያዩ አረብ አገራት ላይ ያለውን "ከፋላ" ተብሎ የሚታወቀውን የስደተኞችን የሰራተኛ ህግ በከፍተኛው ይተቹታል።

ከፋላ ወይም በስፖንሰር አድራጊዎች የሚደገፈው ይህ ስርዓት ሰራተኞቹ ከአሰሪዎቻቸው ፍቃድ ሳያገኙ ከአገር እንዳይወጡና ስራም እንዳይቀይሩ ያስገድዳቸዋል።

ማሪፊ ጨምረውም በአሁኑ ወቅት በኩዌት 15ሺ ያህል ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች እንዳሉ ተናግረዋል።