"ህልም አለኝ":-በቀለ ገርባ

በኦሮምኛ ቋንቋ የተተረጎመው የማርቲን ሉተር ኪንግ መፅሀፍ

'ህልም አለኝ' ወይም አይ ሀቭ ኤ ድሪም በሚለው ታሪካዊ ንግግራቸው የሚታወቁት የጥቁር መብት ተሟጋቹ ማርቲን ሉተር ኪንግ ከተገደሉ 50 ዓመት ሞላው።

በአንደበተ ርዕቱነታቸው የሚታወቁት ማርቲን ሉተር ኪንግ ጥቁሮች ይደርስባቸውም ከነበረው የምእተ ዓመታት ጭቆና ነፃ የሚወጡበት መንገድ በሰላማዊ ትግል ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባዋል በሚል እቅዶችን ነድፈዋል።

ምንም እንኳን ብዙዎች ሰላማዊ ትግል ሲባል ኮሽ ሳይል የሚደረግ ትግል በሚል ቢረዱትም ማርቲን ግን በነጮች የበላይነት የተመሰረተውን ተቋማዊ፣ እምነታዊ ዘረኝነትና ጭቆናን ለመታገል ተቃውሞዎችን ማካሄድ፣ ዘረኛ ህጎችን መጣስንም ያካትታል።

ህይወቱም ይሁን የትግሉ መንገድ ለብዙዎች እንደ ምሳሌነት የሚያዩት ሲሆን ከነዚህም ውስጥ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ-መንበር አቶ በቀለ ገርባ ናቸው።

በተደጋጋሚ ለእስር የተዳረጉት አቶ በቀለ ገርባ በአውሮፓውያኑ 1963 ማርቲን ያደረገውን (አይ ሀቭ ኤ ድሪም) የሚለውን ታዋቂ ንግግር 'ሙለታን ቀባ' (ህልም አለኝ) በሚል ወደ ኦሮምኛ ቋንቋ ተርጉመውታል።

ይህንን መፅሀፍ ለመተርጎም ያነሳሳቸው ቃሊቲ ማረሚያ ቤት በነበሩበት ወቅት ሲሆን ይህም መፅሀፍ እጃቸው እንደገባ ይናገራሉ።

በወቅቱም አንዷለም አራጌም አብሯቸው በእስር ላይ ነበር።

ሀሳባቸውም የነበረው አንዷለም አራጌ ይህንን ታሪካዊ ፅሁፍ ወደ አማርኛ እንዲተረጉመውና እሳቸውም ወደ ኦሮምኛ በመተርጎም ሰፊው ህዝብ እንዲያነበው ማድረግ እንደነበር ይናገራሉ።

"ህዝቦች በሰላማዊ መንገድ እንዴት መብቶቻቸውን ማስከበር እንደሚችሉ የሚያስተምር ነውና እኛም የድርሻችንን መወጣት አለብን" በሚል ስሜት እንደተነሳሱ የሚናገሩት አቶ በቀለ በአጋጣሚ ግን ሳይጨርሱት እንደተለያዩ ይናገራሉ።

ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ትርጉማቸውን አጠናቅቀው ጥቂት ኮፒዎችን ያሳተሙ ሲሆን እንደገና ለእስር በመብቃታቸው በብዛት ባያሳትሙም ከተፈቱም በኋላ መፅሀፉ የተወሰኑ ሰዎች እጅ እንዲገቡ እንዳደረጉ ይገልፃሉ።

የማርቲን ሉተር ኪንግ የሰላማዊ ትግል በኢትዮጵያ ምን ያህል አዋጭ ነው ተብሎ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ በቀለ ሲመልሱ

"ያዋጣል ብቻ ሳይሆን አዋጭ እሱ ብቻ ነው። ወንድምን ወይም የራስን ወገን በመግደል የሚያዝ ስልጣን ዘላቂ ነው የሚል ዕምነት የለኝም" በማለት አቶ በቀለ ይናገራሉ።

ይህ ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ ተደጋግሞ እንደሚነሳ የሚገልፁት አቶ በቀለ ለማርቲን ሉተር ኪንግም ቀርቦለት ነበር።

"እነዚህ ነጮች ነፃነታችንና መብታችንን እንዲሁ የሚሰጡን አይደሉም። መብታችንን ማስከበር የምንችለው በመሳሪያ ብቻ ነው። ነፃነታችንን መጎናፀፍ የምንችለው በዚሁ መንገድ ብቻ ነው" ብለው የተሟገቱ እንዳሉና ከዚህም አለፍ ሲል የግድያ ሙከራ እንደደረሰበት ያወሳሉ።

ለአዋጭነቱም ማሳያዎች ብለው የሚጠቅሷቸውም የስራ ማቆም አድማ፣ ምርቶችና አንዳንድ ተቋማትን ያለመገልገል ማእቀብ ኢኮኖሚያዊ ተቃውሞዎችን ነው

"እነዚህ አድማዎች በሰላማዊ መንገድ የተካሄዱ ናቸው። ለውጥም የሚያመጡ ናቸው። ትልቅ የፖለቲካ አንድምታ ነበራቸውም" ይላሉ።