እነ እስክንድር ነጋ ከእሥር ተፈቱ

እስክነድር ነጋ

የፎቶው ባለመብት, facebook

ያለፉትን አስራ ሁለት ቀናት በእስር ያሳለፉት እስክንድር ነጋና ተመስገን ደሣለኝን ጨምሮ 11 ፖለቲከኞች፣ ጦማሪያንና ጋዜጠኞች ዛሬ ከእሥር መለለቃቸው ተሰማ።

ከተፈችዎቹ መካከል አንደኛው የሆነው ተመስገን ደሣለኝ ወንድም ታሪኩ ደሣለኝ ለቢቢሲ እንደተናገረው ግለሰቦቹ አመሻሽ ገደማ ነው ከእስር የተለቀቁት።

ታሳሪዎቹ ሰኞ ማታ ፍርድ ቤት በጠራቸው ጊዜ ለመቅረብ የራስ ዋስትና ሞልተው ቢፈርሙም እንዳልተፈቱ መዘገባችን የሚታወስ ነው።

በድጋሚ እሥሩ ምክንያትት ለጤና መታወክ ተጋልጦ የነበረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሣለኝ ሆስፒታል ገብቶ ህክምና ካገኘ በኋላ ወደ እስር ተመልሶ ነበር።

ታሪኩ እንደሚለው የተመስገን ጤና መሻሻል ቢያሳይም አሁንም ማስታገሻ መድሃነት እየወሰደ ይገኛል።

የተለቀቁት 11 ግለሰቦች እስክንድር ነጋ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ አንዱዓለም አራጌ፣ አዲሱ ጌታነህ፣ ዘላለም ወርቅ አገኘሁ፣ ማህሌት ፋንታሁን፣ በፍቃዱ ኃይሉ፣ ወይንሸት ሞላ፣ ይድነቃቸው አዲስ፣ ስንታየሁ ቸኮል እና ተፈራ ተስፋዬ ናቸው።

በተመሳሳይ ዘገባ በባህር ዳር ከተማ ታስረው የነበሩ ምሁራን፣ የፖለቲካ መብት አቀንቃኞች እና ፖለቲከኞች በትናንትናው ዕለት መፈታታቸው ይታወሳል።

ከተፈችዎቹ መካከል አንደኛው የሆኑት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምሀሩ አቶ በለጠ ሞላ በእስር ቆይታቸው ወቅት ሲጎበኛቸው በነበረው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ መደነቃቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ካለፈው ወርሃ ሕዳር ጀምሮ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዕውቅናን አግኝተው ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመሥረት ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ያስታወሱት አቶ በለጠ፤ ለእስር መዳረጋቸው እንቅስቃሴያቸውን እንደማይገድበው እና ይልቁንም ፓርቲውን የማወቀር እንቅስቃሴያችውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ለቢቢሲ ገልፀዋል።