የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዘዳንት ጃኮብ ዙማ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ነው

Jacob Zuma, former president of South Africa arrives at the home of the late Winnie Mandela in Soweto, South Africa

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

የጃኮብ ዙማ ክስ መሰማት የሚጀምረው ዛሬ ነው።

ዙማ ፍርድ ቤት የሚቀርቡት እንደ አውሮፓውያኑ በ1990ዎቹ በተደረገ በ2.5 ቢሊዮን በሚገመት የጦር መሳሪያ ግዥ ስምምነት ነው።

ዙማ በደርባኑ ፍርድ ቤት 16 የሚሆኑ ክሶች የሚቀርቡባቸው ሲሆን ክሶቹ ማጭበርበርንና ህገ ወጥ የከፍተኛ ገንዘብ ዝውውርን ይጨምራሉ።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ስልጣን እንዲለቁ የተደረጉት ዙማ ግን ምንም ዓይነት ወንጀል እንዳልፈፀሙ እየተናገሩ ነው።

የፕሬዚዳንቱ ፍርድ ቤት መቅረብ በደቡብ አፍሪካ ዲሞክራሲ የደረሰበትን ደረጃና ባለስልጣናት በፈፀሙት ወንጀል የማይጠየቁበት ዘመን ማብቃቱ አመላካች እንደሆነ ይታመናል።

የዙማ ችሎት ረዥም እንደሚሆን ይታመናል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

ሃሙስ ምሽት ደጋፊዎቻቸው ለዙማ ድጋፋቸውን ለማሳየት አደባባይ ወጥተው ነበር።

በሺዎች የሚገመቱ የዙማ ደጋፊዎች ግን ወደ ደርባኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሄድ ድምፃቸውን እንደሚያሰሙ አስታውቀዋል።

ቀደም ሲል የጀመረው ዙማ ክስ ጉዳይ በተወሰነ መልኩ የደቡብ አፍሪካ ፖለቲካ ላይ ጥላ አጥልቶ የነበረ ቢሆንም በ2009 ለፕሬዝዳንትነት ከመወዳደራቸው በፊት በአገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ክሱ ውድቅ ሲደረግ ነገሮች ረገብ ብለው ነበር።

ለዙማ ያልተኙ ተቃዋሚዎቻቸው ግን ውድቅ የተደረጉት ክሶች ዳግም እንዲንቀሳቀሱ ሲጥሩ ቆይተዋል።በተለይም ዙማ በፓርቲያቸው አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ ኤኤንሲ ያላቸው አቅም ሲቀንስ ተቃዋሚዎቻቸው በርትተዋል።

ከፓርቲያቸው የገጠማቸው ከፍተኛ ከስልጣን ልቀቁ ጫናም ዙማ ከሁለት ወራት በፊት ስልጣናቸውን አስገድዷቸዋል።

የዙማ ቤተሰቦችና ደጋፊዎቻቸው ከዙማ ክስ ጀርባ ያለው ነገር ፖለቲካና እሳቸውን የማጥቃት ዘመቻ እንጂ ሌላ እንዳልሆነ ያምናሉ።