"እንግሊዝ በእሳት እየተጫወተች ነው"ስትል ሩሲያ አስጠነቀቀች

Russia Ambassador to UN
የምስሉ መግለጫ,

በተመድ የሩሲያው አምባሳደር እንግሊዝ በእሳት እየተጫወተች እንደሆነና በዚህም እንደምትፀፀት ተናግረዋል

በተባበሩት መንግስታት የሩሲያ አምባሳደር የሆኑት ቫሲሊ ኔብኒዚያ ከቀድሞ ሰላዩ መመረዝ ጋር በተያያዘ እንግሊዝ የተያያዘቸው ማስረጃ በሌላቸው ውንጀላዎች ሩሲያን ማጠልሸት እንደሆነ ተናግረዋል።

አምባሳደሩ ይህን ያሉት በተመድ የፀጥታው ፍርድ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ነው።

እንግሊዝ ከምረዛ ጀርባ ያለችው ሩሲያ ናት ብትልም ሩሲያ ነገሩን አስተባብላለች።

ሩሲያ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በሚደረገው ምርመራ ልሳተፍ ብትልም ራሷ የድርጊቱ ፈፃሚ ራሷ መርማሪ የሚል አንድምታ ያለው ምላሽ በእንግሊዝ ተሰጥቷል።

የሩሲያው የቀድሞ ሰላይ ሰርጌ ስክራይፓልና ሴት ልጃቸው ዩሊያ ከአንድ ወር በፊት ራሳቸውን ስተው የተገኙት እንግሊዝ ሳልስበሪ ውስጥ ነበር።

የምስሉ መግለጫ,

የ66 አመቱ ስክራፓልና የ33 ዓመቷ ልጃቸው ዩሊያ አሁንም ሆስፒታል ናቸው።

የ66 ዓመቱ አባቷ አሁንም በፅኑ እንደታመሙ ሲሆን ዩሊያ ግን አገግማለች።

ሞስኮ በኒዮርክ የተካሄደውን የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ልዩ ስብሰባ የጠራችው እንግሊዝ ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ መመለስ የሚገባት ነገሮች አሉ በማለት ነው።

በተመድ የሩሲያው አምባሳደር ኒቤነዚያም እንግሊዝ ምንም ተጨባጭ ነገር በሌለበት ሩሲያ ላይ የፕሮፓጋንዳ ጦርነት መክፈቷን ተናግረዋል።

የቀድሞ ሰላዩንና ልጃቸውን ለመመረዝ ጥቅም ላይ የዋለው ኖቫይቾክ ሩሲያ የባለቤትነት መብት ያስመዘገበችበት እንዳልሆነም ይልቁንም በየትኛውም አገር እየተሰራ እንዳለ ገልፀዋል።

"የሆነ ግራ የገባው ቴአትር ነው።የተሻለ ድራማ ሰርታችሁ መምጣት አልቻላችሁም?"በማለት እንግሊዝ እያደረገች ያለውን ነገር ኮንነዋል።

15 አባላት ላለው የፀጥታው ምክር ቤትም ሩሲያ ለምን በጣም አደገኛና ግልፅ በሆነ መንገድ አንድ ግለሰብን መግደል ትፈልጋለች? ሲሉ ጠይቀዋል።

ሰዎችን በመርዛማ ኬሚካል ከመግደል ይልቅ በመቶዎች የሚቆጠሩ ረቂቅ የግድያ ስልቶች ለመኖራቸውን የእንግሊዙ የቴሌቭዥን ተከታታይ ፊልም 'ሚድሳመር መርደርስ' ምስክር እንደሚሆን እስከመጥቀስም ደርሰዋል አምባሳደሩ።