ልማትና የአርሶ አደሮች መፈናቀል በአዲስ አበባ

Qonnaan bulaa fi manneen jireenyaa

"መሬቱን ከኛ ሲወስዱ ጉዳዩን በጥልቀት አናውቅም ነበር። ተተኪ ስራ አልሰጡንም። የተሰጠችንም ገንዘብ ደግሞ እያለቀች ነው" በማለት አርሶ አደር ኃይሉ ከመሬቱ የተፈናቀለበትን አጋጣሚ ለቢቢሲ ያስረዳል።

ከስድስት ዓመት በፊት የአቶ ኃይሉ ደምሴ መሬት በአዲስ አበባ የመሬት አስተዳደር ልማትና ማኔጅመንት በልማት ስም ተወስዶባቸዋል።

22 ሺ ካሬሜትር ስፋት ያለው የእርሻና የመኖሪያ ቤት ቦታ ለአንድ ካሬ በ18 ብር ከ50 ሳንቲም ታስቦ ተከፍሎ እንደተወሰደባቸው አቶ ኃይሉ ይናገራሉ።

የዚህ አርሶ አደር መሬት በከተማው የሚታዪት ትልልቅ የመሰረተ-ልማት ግንባታ ከዋሉት ፕሮጀክቶች መካከል በጋራ መኖሪያ ቤቶችና በረጃጅም ፎቆች ተሸፍኗል።

በእንጨትና በጭቃ የተሰራችው የአቶ ኃይሉ ቤት ካሳ የተበላበት ቢሆንም አሁንም ከቤተሰቦቹ ጋር የክፉ ጊዜ መጠለያው ነች።

ይህ መሬት የሚገኘው በከተማዋ አስተዳደር ስር ስለሆነ ቤቱንም ማሳደስ ሆነ ማስፋፋት አይችሉም።

ይህ ታሪክ የአቶ ኃይሉ ብቻ ሳይሆን በሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ አርሶ አደሮች በተደጋጋሚ የሚያጋጥማቸው ጉዳይ ነው።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ ለልማት ተብሎ 12ሺ አባወራዎች ከቀያቸውና ማሳቸው ተፈናቅለዋል።

የመፈናቀሉን አንድምታ በሁለት መልኩ ማየት የሚቻል ሲሆን አንዱ ለመንግሥት መሰረተ ልማት ማስፋፋት ሲሆን ለአርሶ አደሮች፣ ለሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎችና በአገር ውስጥና በውጭ አገር ለሚገኙ የኦሮሞ ተወላጆች የባህልና ማንነታቸው ጋር መነቀል ነው።

"መፈናቀልና ልማት"

አዲስ አበባ ባሳለፈችበት የምዕተ-ዓመት ጉዞ በአካባቢው ይኖር በነበረው ኦሮሞ ማህበረሰብ መፈናቀልን አስከትሏል። ይህም የአዲስ አበባ ሰፈሮች የኦሮምኛ ቋንቋ መጠሪያ ስያሜ እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል።

ከአዲስ አበባ መልሶ ልማትና ተኃድሶ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በያዝነው ዓመት በአዲስ አበባ 700 ሄክታር መሬት መልሶ ለማልማት እቅድ ተይዟል።

ለዚህ የመሬት ልማት ስራ መሳካት ደግሞ ሁለት ሺ አባወራዎች እንደሚፈናቀሉ የኤጀንሲው ስራ አስኪያጅ አቶ ሚሊዮን ግርማ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ካሳ፣ቅሬታና ፍርኃት

በቦሌ ተወልደው ያደጉት ሌላኛው አርሶ አደር ሲሳይ ነጋሳ ናቸው። የዛሬ 15 ዓመት ወደ አራት ሄክታር የሚጠጋ መሬት ከሳቸውና ካባታቸው ለልማት ተብሎ ተወስዶባቸዋል።

ለመሬቱም ለአንድ ካሬ ሜትር በ3 ብር ከ50 ሳንቲም ተመን ካሳ ተከፍሏቸው ነበር። ይባስ ብሎም ከታሰባላቸውም ካሳ ግብር እንደከፈሉ ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ ከሳቸው የተወሰደ መሬት ላይ እስካሁን ካንድ አቋርጦ የሚያልፍ መንገድ ውጭ ምንም አይነት መሰረተ-ልማት አልተሰራበትም።

አቶ ሲሳይ ነጋሳ ካሉበት የኢኮኖሚ ችግር በተጨማሪ አሁንም እፈናቀላለሁ የሚል ስጋት እንዳላቸው ለቢቢሲ ጨምረው ገልፀዋል።

የተከፈላቸው ካሳ አናሳ መሆን፣ የመኖሪያ ቤት አለመሰጠት፣ የሚመጥናቸው የስራ አለመመቻቸት፣ ለአርሶ አደሮች የመኖሪያ ቤትና የስራ እድል አለመቻቸት እና አስፈላጊ የሆኑ የመሰረተ-ልማት አቅርቦት ለምሳሌ ውሃ ለአርሶ አደሮቹ አለመቅረቡ ከሚያነሷቸው ቅሬታዎች መካከል ናቸው።

ካሳን ጨምሮ ሌሎች ቅሬታዎችን ተቀብሎ ሲያስተናግዱ እንደነበረ የኤጀንሲው ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ግርማ ለቢቢሲ ተናግረዋል። የአዲስ አበባ አስተዳደር በአርሶ አደሮች መፈናቀል የሚከሰቱ ችግሮችን ለማስቆም እየሰሩ እንዳለ ጨምረው ገልፀዋል።

በዚህም መሰረት የአርሶ አደርን የአንድ ካሬ ሜትር ዋጋ ካሳ ወደ 62 ብር ያደገ ሲሆን የግል መኖሪያ ቤት ይዞታ ካሳ ደግሞ 552 ሺ ብር ማደጉን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ቤት መስሪያ ቦታ እንደሚሰጣቸው አክለው ገልፀዋል።

በሌላ በኩል የከተማው አስተዳደር መሬትን ለተጠቃሚዎች በሁለት መልኩ የሚያስተላልፍ ሲሆን የልማት ድርጅቶች እንደ ፋብሪካዎች ላሉት በምደባ ለመኖሪያ ቤትና ለንግድ ቤቶች በሊዝ ይሰጣቸዋል።

ለአርሶ አደሩ የሚከፈለው ካሳ ለሊዝ ከሚፈለው ካሳ ያንሳል ለሚለው ጥያቄ አቶ ሚሊዮን መልስ ሲሰጡ "ከአርሶ አደሩ የሚወሰደው መሬት ለመሰረተ-ልማት ግንባታ ለህዝቡ ጥቅም ስለሚውል በዛ መልኩ ይተላለፋል"

የምስሉ መግለጫ,

አርሶ አደር ኃይሉ ደምሴ

ድንበር

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚዋሰኑበት የተከለለ ምልክት የላቸውም።

ይህ ደግሞ አዲስ አበባ እየሰፋች የሚለውን ቅሬታና ተቃውሞ በማስነሳት ለብዙ ህይወቶች መቀጠፍ ምክንያት ሆኗል።

በአሁኑ ጊዜ የአዲስ አበባ ከተማ ስፋት 52ሺ ሄክታር እንደሆነ ይገመታል።

ይህንን የድንበር ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከኦሮሚያ ክልልና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ ባለሙያዎች ወሰኑን እየሰሩ ነው።

ቢቢሲ እንዳገኘው መረጃ የወሰን ማካለል ስራ በአሁኑ ጊዜ ተጠናቆ የፖለቲካ ኃላፊዎችን ውሳኔ እየጠበቀ ነው።

በዚህ የቴክኒክ ኮሚቴ ስራ አንዳንድ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ያሉ ቦታዎች በኦሮሚያ ስር እንዲሁም በኦሮሚያ ስር ያሉት ደግሞ በአዲስ አበባ እንደተካለሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ለዚህ የማካለል ስራ መስፈርት እንደ ግብዓት ስራ ላይ ከዋሉት ውስጥ የ1987 የተካሄደው ምርጫ ነው።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

የልማት ዋጋ ምን ሊሆን ይገባዋል?