የተዘረፉ ቅርሶች በውሰት መመለሳቸውን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ምላሽ ምንድን ነው?

V&A Museum, Maqdala 1868 display: L: Ethiopian silver leather and amber necklace formerly in the possession of Queen Terunesh R: Gold chalice with incised inscription, made by Walda Giyorgis, Gonder, Ethiopia, 1732-1740 Image copyright V&A Museum
አጭር የምስል መግለጫ የንግስት ጥሩነሽ የአንገት ጌጥና ሙሉ በሙሉ ከወርቅ የተሰራ ዋንጫም ለእይታ ይቀርባሉ።

የእንግሊዙ ቪክቶሪያና አልበርት ሙዚየም ከ150 ዓመታት በፊት በነበረው የመቅደላ ውጊያ በእንግሊዝ ወታደሮች ተዘርፈው የተወሰዱ በወርቅ የተንቆጠቆጠ ዘውድ፣ የሰርግ ቀሚስና የወርቅ ዋንጫዎችን ለአውደ ርዕይ አቅርቧል።

ሙዚየሙን እነዚህን ቅርሶችም ኢትዮጵያ ፍላጎቱ ካላት በውሰት መልክ ሊሰጥ ፈቃደኛ መሆኑን ገልጿል።

ከእነዚህ ቅርሶች መካከል የተወሰኑት እንደ አውሮፓውያኑ በ1868 የተካሄደው የመቅደላ ጦርነት የተዘረፉ ናቸው።

በቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን መስሪያ ቤት የቅርስ ምዝገባና ቁጥጥር ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ ደሳለኝ አበባው እንዳሉት እርሳቸውም ሆኑ ድርጅታቸው ስለጉዳዩ ምንም መረጃ የላቸውም።

በቅርሶቹ ለእይታ መብቃት ላይ ግን ያላቸው አቋም መልካም እንደሆነ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ከኢትዮጵያ የተዘረፉ ቅርሶች በውሰት መመለስ ለብዙዎች ብዥታንና መነጋገሪያን ፈጥሯል። ለዓመታትም ከኢትዮጵያ የተዘረፉ ቅርሶች እንዲመለሱ የተለያዩ ምሁራንም ሆነ ግለሰቦች ሲጥሩ ነበር።

ከነዚህም ውስጥ ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ ከሪቻርድ ፓንክረስት እና ሌሎች ግለሰቦች ጋር በመሆን ብዙ ሙከራዎችን አድርገዋል።

ሙዚየሙ ዛሬ በጀመረው አውደ ርዕይ ላይ የፕሮፌሰር አንድርያስ ምላሽ ኦዎንታዊ ነው።

"ሙዚየሙ በመቅደላ ጦርነት ወቅት የተዘረፉና በእንግሊዝ የሚገኙ ቅርሶቻችን ለህዝብ እይታ የሚበቁበት አጋጣሚ በጣም አናሳ ነው። ስለዚህ ለህዝብ እይታ መቅረባቸው ኢትዮጵያውያንንም ሆነ የኢትዮጵያን ወዳጆች ደስ ያሰኛል ብዬ እገምታለሁ።" ብለዋል

ጨምረውም "እነዚህ ቅርሶች እንዲመለሱ ለመሞገትም ቢሆን ለረጅም ጊዜ በብድር ወደ ኢትዮጵያ ቢመጡ በጣም መልካም ነው። ሀይማኖታዊ፣ ታሪካዊ ወይም ደግሞ ለቅርስጥበቃ የተለየ መነሳሳት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ደስተኛ ይሆናሉ ብዬ አምናለሁ።" ይላሉ

ከዚህ በተጨማሪም በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ኃይለሚካኤል አፈወርቅ በበኩላቸው ቅርሶቹ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ የሚደረገውን ጥረት አካል እንደሆነና ደረጃ በደረጃ ወደዛ የሚወስድ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

Image copyright V&A Museum

መቅደላ ውጊያ ላይ የተመዘበሩት ቅርሶችና ንብረት ብቻ አልነበረም ከዚህም በላይ የሰባት ዓመት እድሜ ያለውን የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ ልዑል አለማየሁ ተጠልፎ ተወስዷል።

ልዑሉ በብቸኝነት ሲሰቃይ ቆይቶም በ18 ዓመቱ እንደሞተ የታሪክ መዛግብቶች ያወሳሉ። የመጨረሻ ጊዜውን አስመልክቶ ከልዑል አለማየሁ አንደበት የተወሰደውን አሉላ ፓንክረስት በፅሁፉ አስቀምጦታል ይህም " ተመርዣለሁ" የሚል ነው።

ተጠልፎ ተወስዶ ህይወቱ ያለፈው የልጅ ልዑል አለማየሁ ህይወት አሳዛኝ እንደሆነ ህይወቱ ላይ የወጡ ፅሁፎች ያሳያሉ።

ከሞተ በኋላ እንኳን አፅሙ ኃገሩ ይረፍ ተብሎም ለእንግሊዝ መንግሥት በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም እስካሁን ምላሽ የለም።

ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ እንደሚሉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ እንግሊዝ በሄዱበት ወቅት ያረፈበትን ቦታ መጎብኘታቸውን ይጠቅሳሉ።

"ይህ ሀሳብ በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ውስጥ ይነሳ እንደነበር አውቃለሁ። ከልዑል አለማየሁም ጋር ቁርኝት አለን። አስክሬኑ ቢመጣም ጥሩ ነው። ያ ደግሞ ልዑል አለማየሁ ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጋር ያለውን ቁርኝት የሚያሳይ ነው። " ብለዋል።

ተያያዥ ርዕሶች