ፒዮንግያንግ ከአሜሪካ ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆኗን ገለፀች

ፒዮንግያንግ ከአሜሪካ Image copyright AFP/Getty Images

ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር ለመወያየትና በሚደረሰው ስምምነት መሠረት የኒውክሌር መሣሪያዎቿን ለማምከን ሁለቱ ሃገራት ባደረጉት ውይይት ላይ ቃል መግባቷን አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን አስታወቁ።

በሁለቱ ሃገራት መካከል የሚደረጉት ውይይቶች በምስጢር የሚያዙና የሁለቱን ሃገራት ከፍተኛ መሪዎች የሚያሳትፉ እንደሚሆኑ ከትራምፕ አስተዳደር ጋር ግንኙነት ያላቸው ምንጮች አስታወቁ።

መቼ እንደሚከናወን ቁርጥ ያለ ቀን ያልወጣለት የሁለቱ ሃገራት ውይይት ምናልባትም ወርሃ ግንቦት ላይ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።

የሁለቱ ሃገራት ውይይት እውን የሚሆን ከሆነ ትራምፕ ከሰሜን ኮሪያ መሪዎች ጋር በመወያየት የመጀመሪያው የአሜሪካ መሪ ይሆናሉ።

ሰሜን ኮሪያ ውይይት ለማካሄድ ዝግጁ መሆኗን ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ ያደረገችው በጎረቤቷ ደቡብ ኮሪያ አማካይነት ነበር።

ልዕለ-ሃያሏ አሜሪካና የኒውክሌር መሣሪያ የታጠቀችው አሜሪካ እንደዚህ ለውይይት ዝግጁ መሆናቸውን ከማሳወቃቸው በፊት የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተው ነበር።

አሁን በእንጥልጥል ያለው ጉዳይ ኒውክሌር የማምከኑ ሃሳብ ነው፤ አሜሪካ ሰሜን ኮሪያ ሙሉ በሙሉ መሣሪያዎቿን እንድታወድም የምትፈልግ ሲሆን ፒዮንግያንግ በዚህ ጉዳይ መስማማት አለመስማማቷ አልታወቀም።

አልፎም አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ ሰሜን ኮሪያን ለንግግር ዝግጁ ናት እያሉ ያሳውቁ እንጂ ፒዮንግያንግ እስካሁን ስለውይይቱ ይፋ አላደረገችም።

ቢሆንም ሁለቱ ሃገራት ከሌሎች ሃገራት ጋር የሚደርጓቸው ውይይቶች እርስ በርስ ለሚያደርጉት ንግግር መንገድ እንደሚጠርግ ብዙዎች ያምናሉ።

ባለፈው የፈረንጆቹ ወር መጨረሻ ገደማ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ወደ ቤይጂንግ ጉዞ አድርገው እንደነበር የሚታወስ ነው፤ ከወዳጃቸው ዢ ሺንፒንግ ጋርም ተወያይተዋል።

ኪም በጥቂት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ በሁለቱ ሃገራት ውይይት ውስጥ ትልቅ ሚና እየተጫወተች ካለችው ደቡብ ኮሪያ መሪ ሙን ጃይ ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል።