የሶሪያ አየር ኃይል ማረፊያ በሚሳይል ጥቃት ደረሰበት

A BBC map showing the locations of Homs and Damascus in Syria

በሶሪያ የሚገኝ የአየር ኃይል ማረፊያ በሚሳይል ከተጠቃ በኋላ ብዙ ሰዎች መሞታቸውን የኃገሪቱ ሚዲያ ዘግቧል

የመንግሥት የዜና ወኪል የሆነው ሳና እንደዘገበው ታይፉር ወይም በተለምዶ ቲ4 ተብሎ የሚታወቀው የአየር ኃይል ማረፊያ ጥቃት የደረሰበት ሰኞ ጥዋት አካባቢ ነው።

ጥቃቱን አድራሹ ወገን ማን እንደሆነ እስካሁን ግልፅ መረጃ የለም።

የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ድንጋጤ ውስጥ የከተተው በታጣቂዎች ስር የምትገኘው ዱማ ከተማን የኬሚካል ጥቃት ተከትሎ የደረሰ ጥቃት ነው።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሶሪያውን ፕሬዚዳንት "እንስሳ" ብለው ከሰደቡት በኋላ ጨምረውም ለሱም ሆነ አጋሮቹ ብለው ለጠሯቸው ኢራንና ሩሲያ " ከፍተኛ የሆነ ዋጋ ያስከፍላችሏል" በማለት ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

በዚሁ እለትም ትራምፕና የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በጋራ መግለጫ ያወጡ ሲሆን " ኃይላቸውን አስተባብረው" ለጥቃቱ አፀፋዊ ምላሽ እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል።

ነገር ግን የአሜሪካ ባለስልጣናት የሚሳይል ጥቃት አላደረስንም በሚል ክደዋል።

"በዚህ ወቅት የመከላከያ ኃይላችን በሶሪያ ላይ የአየር ጥቃት እያካሄደ አይደለም" በማለት ፔንታጎን ባወጣው መግለጫ አትቷል።

"ነገር ግን ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተልነው ነው። የሚካሄዱትንም ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን በመደገፍ ላይ የምንገኝ ስንሆን፤ የኬሚካል ጥቃት የሚያደርሱ ወገኖችንም ተጠያቂ የሚሆኑበትንም ሁኔታ ለመፍጠር እየሞከርን ነው" ብለዋል።

የሶሪያ መንግሥት የዜና ወኪል በታይፉር አየር ኃይል ማረፊያ የደረሰውን የሚሳይል ጥቃት አሜሪካን ተጠርጣሪ አድርጎ ዘግቦ የነበረ ሲሆን ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ግን የአሜሪካን ስም አውጥተውታል።

በባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር የአሜሪካ መንግሥት የሶሪያውን ሻያት የጦር አየር ኃይል ማረፊያ ላይ ተደጋጋሚ የሚሳይል ጥቃት አድርሳለች።

ይህም በታጣቂዎች በተያዘችው ካን ሼኩን ለደረሰው የኬሚካል ጥቃት አፀፋዊ ምላሽ ነው ተብሏል።

በተጨማሪ እስራኤልም በዚህ ዓመትም ከፍተኛ የሚባል የሚሳይል ጥቃት አድርሳለች።

የእስራኤል ጦርም በበኩላቸው በታይፉር ጥቃት ላይ ምንም አስተያየት አልሰጡም።

ዱማ ላይ ምን ተፈጠረ?

የህክምና ባለሙያዎች በምስራቃዊቷ ጉታ ክፍል ቅዳሜ በደረሰው ጥቃት ብዙ ሰዎች እንደሞቱ ገልፀዋል።

ዋይት ሄልሜትስ ተብለው የሚታወቁ ፈጥኖ ደራሽ ቡድን የቀረፁት ቪዲዮ እንደሚያሳየው ቁጥራቸው የማይታወቅ ህይወት የሌላቸው ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች በአንድ ቤት ውስጥ አረፋ እየደፈቁ ታይተዋል።

ነገር ግን ነፃ በሆነ አካል ምን እንደተፈጠረ ወይም የሟቾችን ቁጥር ማወቅ አልተቻለም።

ሶሪያም ይሁን ሩሲያ የኬሚካል ጥቃት ደርሷል የሚለውን ውንጀላ አይቀበሉትም። ዱማን ከተቆጣጠረው ታጣቂ ክፍልም ጋር አካባቢውን ለቆ የመውጣት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ኃይል ስለ ቀውሱ ለመወያየት ለሰኞ ቀጠሮ ይዟል።