ሃውስ ሪዞሉሽን 128 ምን ያህል ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል?

Kongiresii Ameerikaa Image copyright Getty Images

ሃውስ ሪዞሉሽን 128 በመባል የሚታወቀው ሰነድ ዛሬ ለአሜሪካ ምክር ቤት ቀርቦ አልፏል።

ሰነዱ የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ መብትን እንዲያከብር ሊያስገድድ የሚችል እንደሆነና በተለያዩ የኮንግረስ አባላት መረቀቁን መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው የኢትዮ አሜሪካ ሲቪክ ካውንስል የህዝብ ግንኙነት ባልደረባ የሆኑት አቶ አምሳሉ ካሳው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሰነዱ ቁጥራቸው 108 የሚሆኑ ሪፐብሊካንና ዲሞክራት ፓርቲዎች የሚደገፍ መሆኑን የገለፁት አቶ አምሳሉ አዲስ ህግ የተካተተበት ከወትሮው የተለየ ረቂቅ ህግ መሆኑን ይናገራሉ።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ስልጣን ከመያዛቸው ጋር ተያይዞ አገሪቷ ላይ አንዳንድ ለውጦች ሊኖሩ እንደሚችሉ ብዙዎች መጠበቃቸውንም አስመልክቶ የስልጣን ሽግግሩንም በተመለከተ ሰነዱ እውቅና እንደሚሰጡት አቶ አምሳሉ ይገልፃሉ።

"ይህ ረቂቅ ሰነድ መፅደቅ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እውነተኛ የለውጥ ኃዋርያ ከሆኑ ለሳቸው የሚጠቅም ነው። ሰነዱ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያየለ የመጣውን የህዝብ ተቃዉሞ ድምፅ መስማት እንዳለባቸው እንደሚገልፅ ያትታል።" ይላሉ።

ለዓመታት ይህ ሰነድ ሲንከባለል የመጣ መሆኑ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ የውጭ ኃይሎች በአገሪቱ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ የመግቢያ መንገድ ነው በማለት ሲቃወሙት ቆይተዋል።

ሰነዱ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ጉዳያቸው እንዲታይ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ እንዲሁም የአለም አቀፍ ማህበረሰቡ እንዲመረምር የሚጠይቅ ዝርዝር እንዳለው ያስረዳሉ።

ከዚህ ሰነድ በተጨማሪ ሌላ ሰነድ የሚቀር ሲሆን ይህም የውጭ ሀገራት ዲፕሎማቶች እንደልባቸው እንዳይንቀሳቀሱ እንዲሁም በውጭ ሀገራት ያላቸው ንብረትን ንብረትም ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ እንደሆነ በተጨማሪ አቶ አምሳሉ ገልፀዋል።

በዚህም ምክንያት ይህንን ሁኔታ ለማስቀረት የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ጫና ማድረጋቸውንም ጭምር አቶ አምሳሉ ይናገራሉ።

በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ መንግስትን አቋም ለማወቅ ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረትሳይሳካ ቀርቷል።

ተያያዥ ርዕሶች