በአልጄሪያ ወታደራዊ አውሮፕላን ተክስክሶ ቢያንስ 250 ሰዎች ሞቱ

በአልጄሪያ አውሮፕላን ተክስክሶ ቢያንስ 250 ሞቱ Image copyright Reuters

በአልጄሪያ ሰሜናዊ ክፍል የተከሰከሰው ወታደራዊ አውሮፕላን ውስጥ የነበሩ 250 ሰዎች መሞታቸውን የሃገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አስታወቀ።

በአልጄሪያ መዲና አልጀርስ ከሚገኘው 'ቦውፋሪክ' ወታደራዊ አውሮፕላን ማረፊያ በተነሳ ጥቂት ሰዓታት ውስጥ ነው አውሮፕላኑ እንደተከሰከሰ ነው የተዘገበው።

ከሟቾቹ መካከል አብዛኛዎቹ የውትድርና ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎችና ቤተሰቦቻቸው እንደሆኑ የተነገረ ሲሆን ፣10 የበረራ ቡድን አባላትም የአደጋው ሰለባ እንደሆኑ ተነግሯል።

አደጋው በምን ምክንያት እንደተከሰተ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የታወቀ ነገር የለም።

የአልጄሪያ ወታደራዊ ኃይል ዋና አዛዥ የአደጋው መንስዔ እንዲጣራ ያዘዙ ሲሆን ፣ወደ ቦታው በመጓዝ ጉብኝት ለማድረግም ዕቅድ ይዘዋል።

ክስተቱ በአውሮፓውያኑ 2014 ዓ. ም. ተከስክሶ የ298 ሰዎችን ከቀጠፈው የማሌዢያው ኤም ኤች 17 አውሮፕላን አደጋ በመቀጠል የከፋው ነው ተብሏል።

'ኢሉሺን አይ አይ76' በመባል የሚታወቀው አውሮፕላን 'በቻር' ወደተባለች የአልጄሪያ ደቡብ ምዕራባዊ ክፍል ጉዞ እያደረገ ነበር።

ከሟቾቹ መካከል 26ቱ 'ፖሊዛሪዮ' የሚባለው በአልጄሪያ የሚደገፍና በሞሮኮ የሚንቀሳቀስ ነፃ አውጭ ግንባር አባላት እንደሆኑም ዘገባዎች በመጠቆም ላይ ናቸው።